
በሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች የጸጥታ
ችግር መከሰቱ ይታወቃል። የተደራጁ ታጣቂዎች ከሸዋሮቢት ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ዙጢ ከተማ በቅርቡ በፈጸሙት
ጥቃት ሀብትና ንብረት አውድመዋል ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ። ይህንንም ዘጋቢያችን ኤልያስ ፈጠነ በስፍራው ተገኝቶ
መመልከቱን አረጋግጦልናል፡፡
የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪዎችም የጸጥታ ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ነገር ግን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችና የኅብረተሰብ
ክፍሎች ሸዋሮቢት ከተማ በመገኘት ነዋሪዎችን በማረጋጋት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሰርጎ ገቦች እና ተመሳስለው የሚኖሩ አካላት አሁንም የኅብረተሰቡ ስጋት መሆናቸውን አንስተዋል።
በሸዋሮቢት ከተማ ዛሬ ሱቆች፣ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸውንም ነው ነዋሪዎች የተናገሩት።
የአማራ ክልል መንግሥትም አካባቢውን በደንብ ማደራጀትና ማኅበረሰቡ እራሱን እንዲከላከል ማድረግ እንዳለበት ጠቅሰዋል።
ጥቃት በሚያደርሱ አካላት ላይ የማያዳግም ርምጃ በመውሰድም የሕዝቡን ሠላም እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።
በጉዳዩ ላይ በተለይ የአጣዬና የማጀቴ አካባቢ ነዋሪዎችን ለማነጋገር ጥረት ብናደርግም በስልክ ግንኙነት መቋረጥ ምክንያት
አልተሳካም።
የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር እሸቱ ጌታቸው የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች በመንግሥት
የጸጥታ ኀይል ቁጥጥር ሥር ናቸው ብለዋል።
የመንግሥት የጸጥታ አካላትም ኅብረተሰቡን ለማረጋጋት ቅድሚያ ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን አመላክተዋል። አካባቢዎቹን
የማረጋጋትና ወደ ነበሩበት ሠላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m