
“ልጄ መቼ ይሆን ወደ ነበርንበት ወግ ማዕረግ የምንመለሰው?” ከመተከል ዞን የተፈናቀሉ አዛውንት
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሞቀ ቤታቸውን ጥለው ከመተከል ዞን የተፈናቀሉ ዜጎች እንደዛሬው የሰው እጅ
ሳያዩ እነሱም እንደ ሌላው ማኅበረሰብ ግብር እየከፈሉ ለሀገርና ለወገን ይተርፉ የነበሩ ናቸው። ዛሬ የሕዝብና የመንግሥትን እጅ
የሚያዩት ተፈናቃዮች ለዚህ ችግር የተዳረጉት ህይዎታቸውን ለመምራት ጥረት ባለማድረጋቸው ወይም በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት
አይደለም፤ ትርፍ አልባው የፖለቲካ ስሌት የፈጠረው እንጂ። የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል በሚሠራ የፖለቲካ ሴራ ተጎጅ
የሆኑት አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡
የመተከል ዞን ተፈናቃዮች በገዛ ወገኖቻቸው ጉዳት ደርሶባቸው፤ ሀብት ንብረታቸውን ተዘርፈው ነው ወልደው እና ከብደው
ከኖሩበት ቀየ እንዲፈናቀሉ የተደረጉት፡፡
በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ቻግኒ ራንች ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ የሚገኙት ተፈናቃይ እድሜ ጠገብ
አባቶችና እናቶች የተፈጠረው ሁኔታ ባይተዋር ሆኖባቸዋል። በሌላው ዓለም የሚሰሙት የሰው ልጅ መብት ጥሰት በእነሱ ላይ
መድረሱ ከምግዜውም በላይ አሳዝኗቸዋል። በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ አባቶችና እናቶች የምግብ እጥረቱ ብቻ ሳይሆን
ለጤና እክልም ተጋላጭ ሆነዋል፣ ለዘመናት የኖሩበትን አብሮነትም አጥተዋል።
ከዳንጉር ወረዳ ማንቡክ ቀበሌ ተፈናቅለው በቻግኒ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የገቡት ሀጂ አብደላ የሱፍ “ከደረሰብን ችግር
በተጨማሪ ለተፈናቃዩ የሚመጣዉ እርዳታ በቂ አይደለም” ብለዋል። ሀጂ አብደላ የሱፍ እንደነገሩን አንዳንዴ ከክልሉም ሆነ
ከፌዴራሉ መንግሥት የሚመጣዉ ድጋፍ ይዘገያል።
በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙት እድሜ ጠገብ አባቶችና እናቶች በገዛ ወገናቸው ያካበቱትን ሀብትና ንብረታቸውን አጥተው ዕለተ
ሞታቸው እንዲናፍቁ መገደዳቸውን የነገሩን ደግሞ ከድባጤ ወረዳ በርበር ቀበሌ ተፈናቅለው የመጡት ወይዘሮ ወርቄ ሐሰን
ናቸው። ወይዘሮ ወርቄ በድባጤ ወረዳ ተወልደው ኖረዋል። በሕይወት ዘመናቸው ይህን መሰል አደጋ በሰው ቀርቶ በእንስሳት
ሲደርስ እንኳ አላየንም ይላሉ፡፡
ከሚደርስባቸው ውጣ ውረድ በተጨማሪ የስኳር በሽታ ሕመምተኛ መሆናቸዉ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎባቸዋል። “ልጄ
መቼ ይሆን ወደ ነበርንበት ወግ ማዕረግ የምንመለሰው?” ሲሉ የሚጠይቁት ወይዘሮ ወርቄ ትናንት ታፍረው ና ተከብረው የኖሩበት
ዘመን እንደናፈቃቸው ነግረውናል። አሁን ባሉበት ቆይታም ቢሆን መንግሥት በተለይ አቅመ ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችን ነፍሰጡር
እናቶችን እና ሕፃናትን ሳይንገላቱ ልዩ ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ነው የጠየቁት።
በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ተፈናቃዮች የተገኘው ድጋፍ በአግባቡ እንዲደርሳቸው መደረግ አለበት የሚሉት ወይዘሮ ወርቄ
የመጠጥ ውኃ አቅራቢዎችንና የሕክምና ቡድኖች የሚሰሩት ሥራ ምስጋና የሚቸረው ነው ብለዋል።
ከዳንጉር ወረዳ ማንቡክ ቀበሌ የተፈናቀሉት ሼህ ኡስማን ሽፋው የ12 ልጆች አባት ናቸው። ስድስት ልጆቻቸውንም በአካባቢው
ወግ እና ባህል ድረዋል። ከጉሙዝ ወንድሞቻቸው ጋር ተዋድደውና ተረዳድተው እንደኖሩም ተናግረዋል። ይህ ሁሉ መከራ አልፎ፣
ፈጣሪ ላፈናቃዮች ልብ ሰጥቷቸው፣ የተፈጠረው ሁሉ ታሪክ ሆኖ ሀገሩና ምድሩ ለምልሞ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተመኝተዋል።
በአማራ ክልል 495 ሺህ 771 ሰዎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ 407 ሺህ 173 ዜጎች የተፈናቀሉ፤ 88 ሺህ 598
ሰዎች ደግሞ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ከመደበኛ ሥራቸው የተስተጓጎሉና በሚኖሩበት አካባቢ ሆነው ድጋፍ የሚሹ እንደሆነ
በአማራ ክልል የአደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ
ምላሽ ተተኪ ዳይሬክተር ጌቴ ምሕረቴ አስረድተዋል፡፡
ከ407 ሺህ 173 ተፈናቃዮች ውስጥ 59 ሺህ 914ቱ በ18 ካምፖች የታቀፉ ሲሆን 347 ሺህ 259 ተፈናቃዮች ደግሞ
በየወገኖቻቸው ተጠልለው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ ጌቴ ተናግረዋል፡፡
የተፈናቃዮች ቁጥር በየወሩ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ እንደሚችል ያስገነዘቡት ተተኪ ዳይሬክተሩ በየወሩ 61 ሺህ ኩንታል ስንዴ
ወይም ቦቆሎ፣ 183 ሺህ 200 ሊትር ዘይት እንዲሁም 6 ሺህ 107 ኩንታል ክክ ለተጎጂዎች ማቅረብ እንደሚያስፈልግ
አስገንዝበዋል፡፡
በቻግኒ ጊዜያዊ መጠለያ 48 ሺህ 960 ተፈናቃዮች አሉ፡፡ ተፈናቃዮቹ በ74 ድንኳን ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከድንኳኑ ውጪ
ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች በተዋቀረው ግብረኃይል ተጣርተው ድጋፍ የሚደረግላቸው እንደሆነ ተተኪ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ተፈናቃይ በነፍስ ወከፍ በየወሩ 15 ኪሎግራም የምግብ እህል፣ 1 ነጥብ 5 ኪሎግራም ክክና ግማሽ ሊትር ዘይት
እንደሚደርሰው የጠቆሙት አቶ ጌቴ በተፈናቃዮች መጠለያ በርካታ አረጋውያን፣ ነፍሰ ጡሮች፣ ሕፃናት፣ አካል ኩዳተኞች እና
ሌሎች ተጎጂ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለተለዩ ለእነሱ ቅድሚያ በመስጠት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል፡፡
ከፌዴራሉ የሚደርሰው ድጋፍ በሚዘገይበት ወቅት ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች፣ ከበጎ አድራጊ የግልና የእምነት ተቋማት የሚገኝ
ድጋፍ ለተፈናቃዮች እንዲደርስ እንደሚደረግ ነው የጠቆሙት፡፡
ተፈናቃዮች በክረምት ወራት ሊደርስባቸው የሚችልን ችግር ለመቀነስ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ወደ ደረቃማ አካባቢ ለማሸጋገር
ከወዲሁ እየተሠራ መሆኑን አቶ ጌቴ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m