
ለሀገር ዕድገት መሠረት ለሆኑት ሀገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጃፓን፤ ታይላንድና ቻይና የመሳሰሉ ሀገራት በሳይንስና
ምርምር አሁን ለደረሱበት የእድገት ደረጃ መሰረታቸው ሀገር በቀል እውቀቶች መሆናቸው ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያም የበርካታ ሀገር በቀል እውቀቶች ባለቤት ስትሆን እነዚህን እውቀቶች ጠብቆ በማቆየት ረገድ ደግሞ ቤተ እምነቶች
በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
ሀገር በቀል እውቀቶችን በመንከባከብና በተገቢ መንገድ በማጥናት ለሀገር ልማትና ለማህበረሰብ ግንባታ በመጠቀም በኩል ሰፊ
ክፍተቶች እንዳሉም ይነሳል፡፡
ለመሰል ችግሮች መፍትሔ ለማመላከትና እውቀቱን ጠብቀው ላቆዩት ሊቃውንት እውቅና ለመስጠት ያለመ የምክክርና የምስጋና
መድረክም በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ቲሊሊ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በምክክር መድረኩም ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙ ምሁራንን ጨምሮ ከ3 መቶ በላይ የቤተ ክርስትያን ሊቃውንትና ደቀ
መዛሙርት ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ የታደሙ ሊቃውንትም አብነት ትምሕርት ቤቶች ለሀገር ባለውለታዎች ቢሆኑም ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ
የመጥፋት አደጋ እየተጋረጠባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተጋበዙት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላይ ዓለም አሁን ለደረሰችበት የቴክኖሎጂ
ምጥቀት መሰረቱ ሀገር በቀል እውቀት መሆኑን አውስተዋል፡፡
የሀገር በቀል እውቀቶች ምንጭ የሆኑ አብነት ትምሕርት ቤቶች ያሉባቸውን ችግሮች በጥናት በመለየት ለሀገር እድገት ያለቸውን
አበርክቶ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው እንደሚሠራም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የሀሳቡ አመንጪና የፕሮግራሙ አስተባባሪ ወጣት ተስፋሁን ደስታ በበኩሉ ፕሮግራሙ ሀገር በቀል እውቀትን ከትውልድ ወደ
ትውልድ ለማስተላለፍ የሚተጉ ሊቃውንትን ለማመስገንና የእውቀቱ ምንጭ የሆኑ አብነት ትምሕርት ቤቶች ያሉባቸው ችግሮች
በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በመርሃ ግብሩ ማጠናቀቂያም በወረዳው በሚገኙ አድባራትና ገዳማት ለሚያስተምሩ 51 ሊቃውንት የወርቅ ካባና የምስጋና
ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ:– ሳሙኤል አማረ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m