
የበጎ ፈቃደኛ አባላትን ቁጥር ለመጨመር እየሠራ መሆኑን በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ሰሜን ምዕራብ አካባቢ ጽሕፈት
ቤት ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር የሰሜን ምዕራብ አካባቢ ጽሕፈት ቤት
21ኛውን የበጎ ፈቃደኞች ዓመታዊ ስብሰባ አካሂዷል። በስብሰባው በአማራ ክልል በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው የሚገኙ
በጎ ፍቃደኞችም ተገኝተዋል።
ለምለም አወቀ የቤተሰብ መምሪያ በጎ ፍቃደኛ ወጣት ናት። ወጣት ለምለም እንደገለፀችው በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ሴተኛ
አዳሪዎችን ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ስለ ቤተሰብ ምጣኔና የአባላዘር በሽታዎች መተላለፊያና መከላከያ መንገዶችን
ታስተምራለች። ከግንዛቤ ፈጠራ በኋላም ነፃ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብላለች።
በቤተሰብ መምሪያ የዕድሜ ልክ በጎ ፈቃደኛ አቶ ቁምላቸው አይተነፍሱ እንደገለፁት ደግሞ የቤተሰብ መምሪያ ማኅበር
የተቋቋመው በበጎ ፍቃደኛ አባላት ነው፤ እሳቸውም ለብዙ ዓመታት አባል በመሆን አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ
ተናግረዋል።
ሴቶች በሥነ ተዋልዶ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኙ እና የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እንዲጠቀሙ ስልጠና በመስጠትና በማማከር
እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በጎ ሥራ መሥራት ከምንም በላይ እንደሚያስደስታቸው የተናገሩት አቶ ቁምላቸው በቀጣይ
አምስት ዓመታትም በርካታ ዜጎችን አባል በማድረግ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ሰሜን ምዕራብ አካባቢ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ሰሎሞን አጥናፉ ቤተሰብ መምሪያ
ማኅበር በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድና በድህረ ወሊድ ለእናቶች የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በህፃናት ጤናም ትኩረት ስጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ በጎፈቃደኞችም አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የበጎ ፈቃደኛ አባላትን ቁጥር ለመጨመር
እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ሰሜን ምዕራብ አካባቢ ጽሕፈት ቤት አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ መኮንን አይችሉህም (ዶክተር)
“የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ልባቸው በበጎ ምግባር የተሞላ ሰዎች የሚያከናውኑት ተግባር ነው” ብለዋል።
በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚሰጡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በልዩ ሁኔታ ተሰንደው ለተሞክሮነት እየቀረቡ አለመሆናቸውን
ተናግረዋል፡፡ በበጎ ፈቃድ የተሠሩ መልካም ሥራዎችን በተሞክሮነት በመሰነድ በርካታ ዜጎች እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚገባም
አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m