
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ከመጋቢት 15 ጀምሮ ሊካሄድ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተበሰረበት መጋቢት 24/2003 ዓ.ም ጀምሮ
ኢትዮጵያውያን በእውቀት፣ በገንዘብ ፣ በጉልበትና በሞራል ለግድቡ እውን መሆን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ባለፉት 10 ዓመታት 14 ነጥብ 98 ቢሊዮን ብር ከሕዝቡ ለግድቡ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ ለግድቡ
አምባሳደር በመሆን በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ
በፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ግድቡ እየተገነባ መሆኑን እንዲገነዘብ እና የሦስተኛ ወገን ጣልቃ-ገብነት እንዲቀለበስ ሰፊ
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ መሠራቱን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት
ባደረሰን መግለጫ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለግድቡ የሚያደርጉት ድጋፍ ሳይቋረጥ መቀጠሉን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት ኅብረተሰቡ
የታላቁ ህዳሴ ግድብን ቦንድ እየገዛ በአንድ በኩል ግድቡን እየገነባ በሌላ በኩል ደግሞ የቁጠባ ባህሉን በማሳደግ ላይ ይገኛል
ነው ያለው፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በየዓመቱ የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ዕለት በማስመልከት
በመላው ሀገሪቱ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ሲያዘጋጁ መቆየታቸውን ጠቅሷል፡፡ አሁንም ከመጋቢት 15 እስከ መጋቢት 25/2013
ዓ.ም ድረስ ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የቦንድ ሳምንት በመላው ሀገሪቱ እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡ የቦንድ ሳምንት
ማስጀመሪያ መርኃ ግብር መጋቢት 14/2013 ዓ.ም እንደሚኖርም ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች በቦንድ ሳምንት በመሳተፍ ከ50 ብር ጀምሮ ሌሎች
የቦንድ ግዥዎችን በመግዛትና በስጦታ በማበርከት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ለመላው ኢትዮጵያውያን ለታላቁ ህዳሴ
ግድብ 10ኛ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ ብሏል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m