
ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ
አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት
ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር እንደገለጹት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማኅበረሰቡ ሁሉን
አቀፍ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡
እስከ አሁንም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች 15 ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ለታላቁ
ህዳሴ ግድብ ማሰባሰብ መቻሉን ምክትል ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ አንድ ቢሊዮን የሚሆነው ገንዘብ ከውጭ
ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተገኘ ድጋፍ ነው።
ጽሕፈት ቤቱ ከኢምባሲዎች ጋር በመሆን ነው ድጋፉን ማሰባሰብ የቻለው፡፡ ገንዘቡም ከቦንድ ግዥ፣ ከብሄራዊ ሎተሪ፣ ከ8100፣
ከኢትዮጵያ እግር ኳስ እና አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር በመተባበር በተዘጋጁ መርኃ ግብሮች፣ በስጦታ እና የህዳሴ ግድብ ዋንጫን
በማዘዋወር የተሰበሰበ ነው፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከገንዘብ ማሰባሰቡ ባለፈ በውጭ ሀገራት በግድቡ ላይ ሲነሱ የነበሩ የተዛቡ
አመለካከቶችን በሀሳብ የመሞገት ሚናቸው የጎላ እንደነበር ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አንስተዋል። ይሁን እንጅ ዲያስፖራው
ማኅበረሰብ ካለው እውቀት፣ ገንዘብ እና የቴክኖሎጅ ተደራሽነት አኳያ የሚጠበቅበትን ሚና ተጫውቷል ማለት ግን አለመሆኑን
ወይዘሮ ፍቅርተ ነግረውናል።
የግድቡን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ለዲያስፖራው ማኅበረሰብ በማድረስ በኩል ክፍተቶች እንደነበሩም አንስተዋል፡፡ በቀጣይ
በቴክኖሎጂ በመታገዝ ድጋፍ የሚያደርጉበትን አሠራር ለመዘርጋት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ምክትል ዳይሬክተሯ እንዳሉት ለግድቡ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተዘረጋው የቦንድ ሽያጭ ራስን በራስ የማልማት አቅምን ከማሳደግ
ባለፈ የሀገሪቱን የቁጠባ ባህልም እንዲዳብር አድርጓል፤ የሀገሪቱን የቁጠባ መጠንም አሳድጓል፤ በቀጣይ ሀገሪቱ
ለምታከናውናቸው ሌሎች የልማት ሥራዎችም በር የከፈተ ነው።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በፍትሐዊ እና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ እያከናወነች እንደምትገኝም አመላክተዋል።
በዓባይ ላይ ግብጽና ሱዳን ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ የውኃ ሙሌቱ ሥራና ሌሎችም ለግድቡ ለሚደርገው ድጋፍ
የማኅበረሰቡን አንድነት እና ብሔራዊ መግባባትን የበለጠ ያጠናከረ እንደነበር አንስተዋል። በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት ከ 1
ቢሊዮን 122 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ከዚህ በፊት በዓመት ይገኝ ከነበረው ድጋፍ በላይ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከወራት በኋላ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እና የመጀመሪያ ኃይል ማመንጨት ሙከራ የሚከናወንበት በመሆኑ ማኅበረሰቡ ራሱን
ከኮሮና በመጠበቅና ሰላሙን በማስጠበቅ ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 79 በመቶ መድረሱ መገለጹ የሚታወስ ነው።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m