ለ9 ዓመታት አገልግሎት የሰጠው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፓሊሲን ለመቀየር እየተሠራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

141

ለ9 ዓመታት አገልግሎት የሰጠው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፓሊሲን ለመቀየር እየተሠራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ
ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) እየተከለሰ ለሚገኘው ሀገር አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፓሊሲ
ግብዓትና አስተያየት ማሰባሰብ ላይ ያለመ የውይይት መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው። በውይይት መድረኩን
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ አማካሪ ክብርት ፎዚያ አሚን (ዶክተር) ከ1986 ዓም ጀምሮ ለአስራ ስምንት
ዓመታት ስራ ላይ የነበረው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ የተከለሰው ከ18 ዓመት በኋላ በ2004 ዓ.ም ነው ብለዋል፡፡
ፖሊሲው የቴክኖሎጂ ልማትን ከኢኖቬሽን ጋር በሚፈለገው መጠን ያላስተሳሰረ፣ ሥራ ፈጠራን ማዕከል ያላደረገ በመሆኑ
መከለሱ አስፈላጊ እንደሆነ ነው የተጠቆመው። የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማት የመሪነት ሚና እንዲጫወት ፖሊሲውን
መከለስ አስፈላጊ እንደሆነ ዶክተር ፎዚያ ገልጸዋል፡፡ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ረቂቅ የፖሊሲ ሰነዱ ሀገሪቱ ለዘርፉ ትኩረት
በመስጠት እና ምቹ ሥነ-ምህዳር በመፍጠር የሥራ ዕድል እና ሀብት ለመፍጠር ያስችላታል ነው የተባለው።
ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ዕድገት እና የህብረተሰቡን ኑሮ በዘላቂነት የማሻሻል እና ሀገራዊ ብልጽግና ለማምጣት
እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል፡፡ ረቂቅ ሰነዱ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታዎችን አገናዝቦ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን
ልማት ረገድ እራስን ለመቻል ያግዛል ብለዋል። ረቂቁ ለፖሊሲው ዓላማዎቸ ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ለይቶ ያስቀመጠ
ነው ያሉት ዶክተር ፎዚያ፣ እነዚህን የፖሊሲ ጉዳዮችን ለመፍታት መንግሥት የሚከተላቸውን ስልቶች በዝርዝር አመላክቷል።
ረቂቅ ፖሊሲው የሰው ሀብት ልማት፣ የቴክኖሎጂ ልማት፣ ሽግግር እና የእዉቀት አስተዳደር፣ ኢኖቬሽን እና የኢንተርፕራይዞች
ተወዳዳሪነትን፣ ምርምርና ልማት፣ ጥራትና አዕምሯዊ ንብረት፣ የፋይናንስ አቅርቦት መዋዕለ-ንዋይ- ድጋፍና ማበረታቻ፣ ትብብር
እና ትስስር እንዲሁም አካባቢዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማትን በዋና ዋና የፖሊሲ ጉዳይነት መለየቱን ግልጸዋል፡፡ ምንጭ፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሠላማዊ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደሚሠሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተናገሩ፡፡
Next article‹‹በየአካባቢው የሚፈጸሙ ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙና ሀገራዊ አንድነት እንዲጎለብት ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል›› የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን