የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ከጥላቻ ንግግር በጸዳ መልኩ መሆን እንዳለበት የሕግ ምሁር ገለጹ፡፡

236

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ከጥላቻ ንግግር በጸዳ መልኩ መሆን እንዳለበት የሕግ ምሁር ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት 28/2013 ሀገራዊ ምርጫ ታካሂዳለች። ይህን
ተከትሎ ዕጩ ተወዳዳሪዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው ከተለያዩ ቦታዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ናቸው።
የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያካሂዱ ዕጩ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው ከጥላቻ ንግግር በመውጣት የያዙትን የፖሊሲ
አማራጭና የስትራቴጂ አቅጣጫ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውም የሕግ ምሁራን ይመክራሉ።
በተለይም ዕጩ ተወዳዳሪዎችና አባሎቻቸው ከጥላቻ ንግግሮች የጸዳ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ማከናወን እንዳለባቸው ነው
የሕግ ምሁራን ያስገነዘቡት፡፡
አቶ ፈንታ ታረቀኝ በአማራ ክልል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ናቸው። እንደ አቶ ፈንታ ማብራሪያ የጥላቻ ንግግር ማለት በአንድ ሰዉ
ወይም የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሔርን፣ ብሔረሰብንና ሕዝብን፣ ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን
መሠረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው፡፡ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው
ሠላማዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር
አዋጅ ቁጥር 1162/11 ዓ.ም የተደነገጉ ሕጎችን በጥንቃቄ ማክበር እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
በአዋጁም ዕጩ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው ማከናወን የሚገባቸውና የማይገባቸው ጉዳዮች በግልፅ
መቀመጣቸውን አቶ ፈንታ ጠቁመዋል፡፡ በሥነ ምግባር ደንቡ መሠረት ዕጩ ተወዳደሪዎችና አባሎቻቸው የሌሎች ሰዎችን መብት
በማይነካ መልኩ የራሳቸውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማኅበረሰቡ ማስተዋወቅ አንዱ ማከናወን የሚገባቸው ትልቅ ተግባር መሆኑን
አስረድተዋል፡፡
በቅስቀሳ ወቅትም አንድ ዕጩ ፓርቲ ወይም የዕጩ ፓርቲው አባል በሌላው ዕጩ ተወዳዳሪ ላይ የጥላቻ ንግግር ማራመድ በሕግ
ተጠያቂ እንደሚያደርገውም የሕግ ምሁሩ ተናግረዋል። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ዕጩ ተወዳዳሪዎችና አባሎቻቸው የሌላውን
ዕጩ ተወዳዳሪ መብት ማክበር የማይችሉ ከሆነ በምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/11 ዓ.ም መሠረት የአስተዳደራዊና
የወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡
እናም ዕጩ ተወዳዳሪዎችና አባሎቻቸው በሌላው ዕጩ ተወዳዳሪ ዘርን፣ ቋንቋን፣ ማንነትን፣ ሃይማኖትንና ሌሎችን መሠረት
በማድረግ የጥላቻ ንግግሮችን ማራመድ ተገቢነት እንደሌለውም ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ፈንታ ገለፃ አንዱ ዕጩ ተወዳዳሪ በሌላው ዕጩ ተወዳዳሪ የሚያራምደው የጥላቻ ንግግር ሁሉም ዕጩ ተወዳዳሪዎች
በእኩል ሜዳ የምረጡኝ ቅስቀሳ ለሕዝብ እንዳያደርሱና ሕዝቡም የራሱን ይሁንታ እንዳያስቀምጥ እንቅፋት ይፈጥራል።
“ከአንድ ዕጩ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ጀርባ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መኖራቸውን በማሰብ ዕጩ ተወዳዳሪ የፖለቲካ
ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ከጥላቻ ንግግር በጸዳ መልኩ መሆን አለበት” ሲሉ ነው መልእክት ያስተላለፉት፡፡ ሁሉም
ዕጩ ተወዳዳሪዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጥላቻ ንግግር ራሳቸውን እንዲያቅቡም መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleካናዳ 132 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ለአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ልታበረክት ነው፡፡
Next article338 ዜጎች ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ