
የጨጨሆ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር በሁለት ወራት ውሥጥ እንደሚፈታ የነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር ውኃና ፍሣሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት አሥታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) እናቶች፣ አቅመ ደካሞች እና ህጻናት ከአቅማቸው በላይ ጀሪካን በጀርባቸው ተሸክመው ዳገት መውረድና መውጣት የተለመደ ነው። ልጃገረዶች በሌሊት ተነሥተው በየወንዙ ይንከራተታሉ። አዛውንቶች በመጦሪያ ጊዜያቸው ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምረው ከወጣቶች ጋር በድቅድቅ ጨለማ ይጓዛሉ፤ እስከ ጥዋት ሦስት ሰዓትም ውኃ ለመቅዳት ተራ መጠበቅ ግድ ይላቸዋል። ተራው ከደረሣቸውም በዛለ ሠውነታቸው ጀሪካን በጀርባቸው ተሸክመው ተንደርድረው የወረዱትን ዳገት ተጨንቀው ይወጡታል። ተራ ሳይደርሣቸው ውኃው ካቋረጠ ደግሞ ህይወት ነውና አንድ ጀሪካን ውኃ በ6 ብር ይገዛሉ። አካባቢው ካለው የመሬት አቀማመጥ አኳያ የከርሰ ምድር ውኃ ማግኘት አስቸጋሪ ነው።
በላይ ጋይንት ወረዳ ጨጨሆ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አዘነግ ደምሴ የሚተዳደሩት ጠላ በመጥመቅ ነው። ለሥራቸው ደግሞ በትንሹ በቀን እሥከ አምሥት ጀሪካን ውኃ ያሥፈልጋቸዋል። ይህንንም ለማግኘት ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ እንድ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ቁልቁለታማ ቦታ በመውረድ የውኃ ተራ ይይዛሉ። በሌሊት ተጉዞ አንድ ጀሪካን ውኃ ለማግኘት አሥቸጋሪ በሆነበት ቦታ አምሥት ጀሪካን ቀድቶ ጠላ መጥመቅ የማይሞከር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተሰብ ለማሥተዳደር ፈተና ሆኖባቸዋል። አንድ ጀሪካን ውኃ ለማግኘት አምሥት ሰዓት ከወሰደ ለሁለት እና ሦስት ጀሪካን ለማግኘት መዋል ማደር ግድ እንደሚል ነግረውናል። በዚህም ያለምንም ሥራ ውኃ ለመቅዳት ተራ በመጠበቅ ጊዜው ያልቃል።
ሌላኛዋ የጨጨሆ ነዋሪ ተማሪ ብርቱካን አንለይ እንዳለችው ተማሪዎች ከነዋሪዎች ቀድመው ውኃ መቅዳት ካልቻሉ ትምህርት ቤት መሄድ የማይታሠብ ነው። ቀድሞ ለመቅዳት ከሥምንት ሰዓት ጀምሮ መጓዝ ግድ ይላል። ከነዋሪው ቀድሞ መቅዳት ካልተቻለ ደግሞ ከትምህርት ቤት መልስ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ተራ ጠብቀው ለመቅዳት እንደሚገደዱ ነግራናለች። ይህ ደግሞ በትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
በተለይ የሚያጠቡ እናቶች እና አቅመ ደካሞች ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ወድቀዋል፣ የሚያገኙት ውኃ ከመጠጥ ባለፈ ለንጽህና እና ለሌሎች አገልግሎቶች ለማዋል የማይታሰብ ነው፤ የንግድ ድርጅቶች ከሌላ አካባቢ አንድ ጀሪካን ውኃ በ6 ብር በመግዛት ሥራቸውን እንደሚሠሩም ነግራናለች።
የላይ ጋይንት ወረዳ ውኃና ኢነርጅ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አሰፋ ደስታ እንደገለጹት የጨጨሆ ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ የውኃ ችግር ገጥሟቸዋል። በተለይም ደግሞ በእናቶች፣ በተማሪዎች፣ በአቅመ ደካሞች፣ ውኃን መሠረት አድርገው በሚተዳደሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተጽዕኖ አሣድሯል።
ችግሩን ለመቅረፍ በክልሉ መንግሥት የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ ሰኔ/2007 ዓ.ም ተጀምሮ የካቲት/2008 ዓ.ም ቢጠናቀቅም በመሬት መንሸራተት ምክንያት አገልግሎት መሥጠት አልቻለም። በዚህ ዓመት የነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር ውኃና ፍሣሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ጉዳት የደረሠበትን መሥመር የመቀየር ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በሁለት ወራት ውሥጥም ችግሩ እንደሚፈታ ነግረውናል።
ውኃው የሚሣበው ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ጎብጎብ ተብሎ ከሚጠራ ቦታ ነው፡፡ በሰከንድ 12 ነጥብ 5 ሊትር የማመንጨት አቅም አለው። በጨጨሆና ጋንጋ የሚኖሩ ከ8 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችንም ተጠቃሚ ያደርጋል። የመሥመር ዝርጋታ ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል። 100 ሺህ ሊትር ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ማጠራቀሚያ እና የ20 ቦኖዎች ግንባታም ተጠናቋል ብለዋል፡፡ ለሥራው 25 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበትም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ