
ሰላማዊ ሰልፎቹ በሰላም ተጠናቅቀዋል፡፡
ዛሬ መስከረም 4/2012 ዓ.ም በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
በጎንደር፣ በወረታ፣ በደብረ ታቦር፣ በመቄት፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በነፋስ መውጫ፣ በመካነ እየሱስ፣ በመካነ ሰላም በምዕራብ በለሳ፣ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ እና በሌሎችም ከተሞች ነው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታይ ምዕመናን ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሄዱት፡፡

ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ፣ ግፍ እና መሰደድ በተመለከተ በሰልፎቹ ድምጻቸውን አስተጋብተዋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፎቹ ከተላለፉ መልዕክቶች መካከል፡-
•“ቤተ ክርስቲያንን ያቃጠሉ፣ ምዕመኖቿንም የገደሉ፣ በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ!”
• “መንግስት የተቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያናት በአስቸኳይ ያሰራ!”
• “ሀገርን ከነድንበሩ፣ ነጻነትን ከነክብሩ፣አንድነትን ከነጀግንነቱ፣ለሀገር ያስረከበች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህ ፈጽሞ አይገባትም!” የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ሰላማዊ ሰልፎቹ በሰላም እንደተጠናቀቁም ከየአካባቢዎች የሚገኙት ዘጋቢዎቻችን መረጃ አድርሰውናል፡፡