
አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ወቅቱን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተዘጋጀ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) ትምህርት ሚኒስቴር አዲሱን የአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓተ-ትምህርት ለማሻሻልና የመጨረሻ ቅርጽ አስይዞ ወደ ተግባር ለማስገባት አውደ ጥናት እያካሄደ ነው። አውደ ጥናቱ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት አምስት ዩኒቨርሲቲዎችን በማሳተፍ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
መድረኩ ቀደም ሲል የተሰበሰቡ ግብዓቶችን መሰረት በማድረግ የአዲሱ የአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓተ-ትምህርት ለማሻሻልና የመጨረሻ ቅርጽ አስይዞ ወደ ተግባር ለማስገባት ያለመ ነው።
የትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ተወካይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዛፏ አብርሃ የሥርዓተ-ትምህርት ማሻሻያው ባለፉት ጊዜያት ከአንደኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል የነበሩትን የሥርዓተ ትምህርት ችግሮችን ሊቀርፍ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሥርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት የይዘት ፍሰቱ፣ ተፈላጊ የመማር ብቃት መለኪያና ሰነዶች በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ያሉ የብቃት ማረጋጋጫ ተቋማት ተሞክሮዎችን በመውሰድ የተገመገመ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዝግጅቱ በሂደት ላይ ያለው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተማሪ በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ እንዲሆን የግብረገብ ትምህርትን ያካተተ ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ለተማረ ዜጋ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሏል።
በሥርዓተ ትምህርቱ አዘገጃጀት ሂደት የቋንቋ፣ የሂሳብ፣ የሳይንስና የማኅበራዊ ትምህርት ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከአምስቱ ከፍተኛ ትምህርት የልዕቀት ማዕከላት የተውጣጡ የዘርፉ ምዑራን፣ ባለሙያዎችና የሲቭል ማኅበራት ተሳታፊ ሆኖዋል።
ለአዲሱ ሥርዓተ ትምህርቱ ማሻሻያ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ከተጠናቀቀ በኋላ ለትግበራ ወደ ክልሎች እንደሚላክ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
