የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በየአጥቢያዎቹ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ጸሎተ ምህላ አወጀ፡፡

384

ባሕር ዳር፡ መስከረም 3/2012 ዓ.ም (አብመድ) ሀገረ ስብከቱ ለመስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ከፊታችን ሰኞ መስከረም 5 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ጸሎተ ምህላ አውጇል፤ ለመስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቷል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመላከተው የፀሎተ ምህላው ዓላማ በቤተ ክርስቲያኗ እና በምዕመኖቿ ላይ የሚደርሰውን መከራ፣ ግፍ እና መሰደድ አስመልክታ ለፈጣሪዋ መልዕክት ለማቅረብ ነው፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫውን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው የሰጡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም ኦርቶዶክስ ለሀገር ባለውለታ መሆኗ ተረስቶ እና ተዘንግቶ ቤተ ክርስቲያኗ ለጥቃት፤ ምዕመኖቿ ለእንግልት እየተጋለጡ ነው ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ በየጊዜው እየተፈጠረ ያለውን ጥቃት ስለሃገር አንድነት፣ አብሮነት እና ሰላም ስትል በትዕግስት ብታየውም ጥቃቱ ከመቆም ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ እና እየሰፋ መጥቷል ነው ያሉት፡፡ ጥንታዊት፣ ታሪካዊት፣ ሐዋሪያዊት እና ብሔራዊት በሆነችው ቤተ ክርስቲያን እና በአገልጋዮቿ ላይ ብሄርን መሠረት ያደረገ እና ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈፀመ ነው ያሉት መልአከ ሰላም ኤፍሬም ለተከታታይ ሰባት ቀናት በሃገረ ሰብከቱ ሁሉም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ከምሽቱ 11፡30 ጀምሮ ጸሎተ ምህላ እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡

በሰባተኛውም ቀን እሁድ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም የፀሎተ ምህላው ማሳረጊያ እና ሰላማዊ ሰልፍ ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡ እሁድ በሚኖረው ሰልፍ በሦስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የማጠቃለያ ጸሎተ ምህላ ይኖራል ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ መልአከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን ናቸው፡፡ መልአከ ብርሃን ፍስሃ እንደገለጹት ምዕመኑ ጠዋት 2፡00 ሰዓት በመስቀል አደባባይ ቅዱስ ፊሊጶስ ገዳም ይሰባሰባሉ፤ መነሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ ወደ አዝዋ፣ ከአዝዋ ወደ ፓፒረስ፣ ከፓፒረስ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ጉዞ ይደረግና በቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል የመጀመሪያ ጸሎተ ምህላ ይደረጋል ተብሏል፡፡

የመጀመሪያው ጸሎተ ምህላ እንደተጠናቀቀ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል በዴፖ፣ ከዲፖ ወደ ኖክ በሚወስደው መስመር በመጓዝ በደብረ ምህረት ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ጸሎተ ምህላ ይደረጋል፡፡ ከደብረ ምህረት ቅድት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ወደ ኖክ ከዚያም ወደ መስቀል አደባባይ ቅዱስ ፊሊጶስ ገዳም ሦስተኛው ጸሎተ ምህላ ተደርጎ እና በአባቶች ጸሎት መርሃ ግብሩ ተዘግቶ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

በሰልፉ የሚተላለፉ መልዕክቶችም ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸው እና በቤተ ከርስቲያኗ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል፡፡ ስለ መርሀ ግብሩ ለክልሉ መንግስት እና ለባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር የሚመለከታቸው አካላት እውቅና ተፈጥሯል ያሉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሐፊ መንግስት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

ከጸሎተ ምህላው እና ከሰልፉ በኋላ በእለቱ 10፡00 ሰዓት ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ስለወቅታዊው የቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ውይይት ይደረጋል ተብሏል በመግለጫው፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleየአማራ ሕዝብ በ2012 በአንድነት በመቆም ድህነትንና የህልውና ፈተናዎችን የሚወጣበት እንደሚሆን ተገለጸ፡፡
Next articleሰላማዊ ሰልፎቹ በሰላም ተጠናቅቀዋል፡፡