
“ላለፉት ሦስት ዓመታት በተካሄደ የፖለቲካ ሪፎርም አሁን ላይ ራሳቸውን የቻሉ ገለልተኛ ተቋማትን ለመመስረት አስችሏል”
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ፣ የሰብዓዊ
መብት አያያዝ እና የሕግ የበላይነት ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል፡፡ ውይይቱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ ማሻሻያ
ለዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትና የዲሞክራሲ ተቋማት ለማስገንዘብ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓትና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በተወሰደው
የሪፎርም ማሻሻያ የፍርድ ቤቶችን ነጻነት እና ገለልተኝነት እያረጋገጡ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል
የተወሰዱ እርምጃዎች ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤቶች አይነኬ የተባሉ የመንግሥት ውሳኔዎችን ጭምር በፍርድ ቤቶች የሕግ
አግባብነታቸውን ላይ ክርክር ማድረግ መጀመራቸውን አውስተዋል፡፡
የፍትሕ ሥርዓቱ ከመዋቅራዊ ማሻሻያው በተጨማሪ አግባብነት ያላቸውን አጋዥ የሕግ ማሻሻያዎችንም እያደረገ መሆኑን
ፕሬዝዳንቷ አስረድተዋል፡፡
ወይዘሮ መዓዛ የሕግ የበላይነትን በማስፈን ረገድ የተቋሞቹን ተዓማኒነት ለማሰረፅ የሕግ ተቋማቱን አወቃቀር በአዲስ መልክ
መደራጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡
መጪውን ሀገራዊ ምርጫን በማስመልከት በሰጡት ማብራርያ ፍርድ ቤቶች ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በቅድመ እና ድህረ
ምርጫ የሚከሰቱ ውዝግቦችን ለመፍታት ከመደበኛው ፍርድ ቤት ውጭ ራሳቸውን የቻሉና በምርጫ ላይ ብቻ ያተኮሩ ገለልተኛ
ፍርድ ቤቶች መቋቋማቸው አስታውቀዋል፡፡ እነዚህ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት በገለልተኛነት ውዝግብን በሕግ አግባብ ብቻ
የመፍታት ዝግጁነት ለተደረሰበት ማሻሻያ ማሳያ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻውን መጠናቀቅ ተከትሎ የፍርድ ቤቶች ሁኔታ ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ
እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ መሰረተ ልማቶቹን መልሶ የመገንባት ሥራ እየተካሄደ በመሆኑ የፈረሰውን መዋቅር በማስተካከል
የፍርድ ቤቶች ሥራ እንደሚጀምር ገለጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶክተር) በሀገር ውስጥ ያለው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ
ሁኔታዎችን በአግባቡ እንዲከናወኑ ከተካሄደው ሪፎርም በኋላ በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ በተለይም
የፖለቲካ፣ የሲቪክ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙኃን ምህዳር እየሰፋ መምጣት ችግሮችም ቢኖሩ በተለየ ሁኔታ በነጻነት ሥራቸውን
እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡
በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ መሬት ያለውን ሃቅ ሳይረዱ ዓለም አቀፍ ተቋማት በችኮላ የሚያወጧቸው መረጃዎች ከጥቅሙ
ጉዳቱ እንደሚያመዝንም አሳስበዋል፡፡ ኮሚሽነሩ በሀገር ውስጥ ለሚፈጠር የመብት ጥሰቶች የውጭ አካላት ገብተው
ማጣራታቸው እንደመፍትሄ ሊታይ አይገባም ብለዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ተቋማት ምርመራ እንዲያካሂዱ ቅድሚያ መሰጠት እና
ውጤቱንም መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሌላ ሀገር እንደሚደረገው በመንግሥት በጀት የሚተዳደር ተቋም ቢሆንም በሥራው ግን
የማንኛውንም ወገን ጣልቃ ገብነት የማያስተናግድ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ “ላለፉት 27 ዓመታት ተቀብረው የነበሩ ተቋማት ላለፉት ሦስት ዓመታት
በተካሄደ የፖለቲካ ሪፎርም አሁን ላይ ራሳቸውን የቻሉ ገለልተኛ ተቋማትን ለመመስረት አስችሏል” ብለዋል፡፡ በተለይም የሕግ
የበላይነትን ለማስፈን እየተካሄደ ያለው ተሃድሶና የሰብዓዊ መብት ተቋማት የማጠናከር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በዋስትና ከእስር ቤት በፍርድ ቤቶች ትእዛዝ እንደማይወጣ አምባሳደር ተፈሪ
አስታውሰዋል፡፡ ሕግ በማስከበር እርምጃው ተጠርጥረው የተያዙ በፍርድ ቤቶች በዋስትና መለቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡
በትግራይ ክልል የተካሄደውን ሕግ የማስከበር እርምጃ ተከትሎ ተፈጽመዋል የተባሉ ማንኛውንም የሕግ ጥሰቶች በኢትዮጵያ
ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመሬቱ ላይ ተገኝተው ምርመራ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር
ግን ችግሮች ቢኖሩ ከማንኛውም አፍሪካዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ምርመራ ለማድረግ መንግሥት ሙሉ
ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በውጤቱ ላይ ተመስርቶም አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁነቱን አረጋግጠዋል፡፡
በቀጣይም በልዩ ልዩ ዘርፎች እየተካሄደ ያለው መሰረታዊ የሪፎርም ሂደቶችን በማስገንዘብ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እና
ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ክራይስስ ግሩፕ ምክትል ፕሬዝደንት እና የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ኮምፎርት ኢሮ በውይይቱ እንዳነሱት
የማሻሻያ ሂደቱ ሽግግር ላይ በመሆኑ በዚህ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ያጋጥሙታል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
አሕመድ የጀመሩት የሪፎርም ሥራ በሂደት ላይ እንዳለ እንደሚገነዘቡ መግለጻቸውን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያደረሰን መረጃ
ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
