
ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በቴሌኮምዩኒኬሽን ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ተስማሙ።
ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጂቡቲ
የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በጂቡቲ የፖስታ እና ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ራድዋን አብዲላሂ ባህዶን ጋር ተገናኝተው
ውይይት አካሂደዋል፡፡ ሀገራቱ በቴሌኮምዩኒኬሽን መስክ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር በሚረዱ ጉዳዮች ላይም መክረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮምን ዘርፍን ለማሻሻል እየወሰደ ስላለው እርምጃ
ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተለይም ሁለት ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች በቴሌኮም ኦፕሬተርነት እንዲሳተፉ ጨረታ መውጣቱንና ጨረታውም እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 5
ቀን 2021 እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው ሂደትም በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የቴሌኮምዩኒኬሽን
ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን አሳይተዋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም ኢትዮ-ቴሌኮም ስትራቴጂካዊ አጋር እንዲኖረው ያለው ድርሻ 40 በመቶ ለሽያጭ እንዲያቀርብ መንግሥት
መወሰኑንና ለዚህም የዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ እያደገ በሚመጣበት ወቅት ጂቡቲ በቴሌኮምዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ይበልጥ በመሳተፍ ተጠቃሚ
እንደምትሆንና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የቴሌኮም ትራፊክ ደኅንነት በማስጠበቅ ሂደት ውስጥ ጂቡቲ ወሳኝ ሚና
እንደሚኖራት ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
በጂቡቲ የፖስታ እና ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ራድዋን አብዲላሂ ባህዶን እንደተናገሩት የጂቡቲ መንግሥት የቴሌኮም
ዘርፍን በማጠናከርና በማዘመን የምስራቅ አፍሪካን የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ሁለቱ ሀገራትም በኢኮኖሚ፣
በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን
ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
