በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የሚኖሩ አማራዎች አሁንም የጸጥታ ስጋት ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 06/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ እና በምሥራቅ ወለጋ ዞኖች በተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት አድርጎ በተፈጸመ ጥቃት አማራዎች መገደላቸውን እና በስጋት አካባቢያቸውን ለቅቀው መውጣታቸውን ዘግበናል፡፡
ዛሬም አብመድ የአካባቢውን ነዋሪዎች ስለሁኔታው ጠይቋል፡፡ ችግሩ በተለይ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ጃርዴጋ ጃርቴ ወረዳ መቀጠሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ትናንትም አምስት ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡ በአቤ ደንጎሮ ወረዳ የሚኖሩ አማራዎችም አሁን ላይ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ “በወረዳው የካቲት 28 እና 29/2013 ዓ.ም ግድያ ሲፈጸም የጸጥታ አካላት ፈጥነው አልደረሱልንም” ብለዋል ነዋሪዎች፡፡
በዚህም አማራዎች ተገድለዋል፤ ተፈናቅለዋል፤ በርካቶች ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው በመሸሽ ጫካ ውስጥ የሚገኙትም ለከፍተኛ እንግልት መጋለጣቸውን አንስተዋል፡፡ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን ያልጠቀስነው አንድ አስተያዬት ሰጪ የጸጥታ ኀይል መግባቱ እየተነገረ ቢሆንም እሳቸውን ጨምሮ በርካታ አማራዎች በስጋት ምክንያት ቤታቸው እንደማያድሩ ተናግረዋል፡፡
“ባለንበት ቦታ መጥተው ጥቃት ከፈጸሙብንም መከላከል የምንችልበት አቅም የለንም” ብለዋል፡፡ በዚሁ ወረዳ የጸጥታ ኀይል ገብቶ አካባቢውን እያረጋጋ መሆኑን የተናገሩ ሰዎችም አሉ፡፡ ይሁን እንጂ የጸጥታ ኀይሎች በከተማ ብቻ የተወሰኑ በመሆኑ ከከተማ ውጭ ያለው ኀብረተሰብ ስጋት ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነት ተኮር ግድያ እየተፈጸመ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህንን አስመልክቶ የክልሉ መንግሥት የሠላምና ደኅንነት ቢሮ እና የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ማብራሪያ እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም፡፡ በጉዳዩ ላይ መጋቢት 01/2013 ዓ.ም የሥራ ኀላፊዎቹ ስልክ ባለማንሳታቸው ሀሳባቸውን ማካተት እንዳልቻልን ገልጸን ነበር፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
