
ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 6/2011 ዓ.ም(አብመድ) የህልውና ፈተናዎችን ለማሸነፍና ቅጥ ያጣውን የሀገሪቱን ፖለቲካ ለመግራት የአማራ ሕዝብ በጠንካራ አንድነት ላይ እንዲቆም ተጠየቀ።
የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው በቅርቡ ሥራ የጀመሩት አቶ ጌትነት ይርሳው ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአማራ ሕዝብ በ2012 በአንድነት በመቆም ድህነትንና የህልውና ፈተናዎችን የሚወጣበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ለራሱ መብት መከበር ባለፉት ዘመናት በአንድነት ባለመቆሙ በርካታ ችግሮች ደርሰውበታል ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ የሰላም እጦት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በጋራ መቆም ይኖርበታል ብለዋል፡፡
“ቀደምት አባቶች በአንድነት ነፃ ሀገርንና ትልቅ ታሪክን ማውረስ ችለዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በጠንካራ አንድነት ላይ ተመስርቶ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቹ ለማውረስ አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ መጀመር አለበት” ብለዋል አቶ ጌትነት፡፡ የአማራ ሕዝብ የህልውና ፈተናዎችን ማሸነፍና ቅጥ ያጣውን የሀገሪቱን ፖለቲካ መግራት የሚችለው በጠንካራ አንድነት ላይ በመመስረት እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
“ሕዝብ ያልደገፈው መሪ ሥሩ የተነቀለበት ዛፍ ነው” ያሉት አቶ ጌትነት በሀገሪቱ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ፍትሐዊ እኩልነት እንዲረጋገጥ የአማራ ሕዝብ ከክልሉ መንግስት ጎን ሆኖ እንደሚቆም አስታውቀዋል፡፡
የመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአማራ ሕዝብ አንድነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የጥንካሬ ምንጭ በመሆኑ በያሉበት የሰው ልጆችን ጥቅም መሠረት ያደረገ ሥራ በመሥራት ለሀገሪቱ ብልፅግና የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ጌትነት ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ጌትነት በመግለጫቸው ለመላው የአማራ ሕዝብ፣ ለአማራ ተወላጆች፣ ለኢትዮጵያውያን እና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2012 ዓ.ም በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ