
የ2013 ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን ኢዜማ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) በ2013 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ
ፍትህ (ኢዜማ) የምረጡኝ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል፡፡
በባሕር ዳር እና አካባቢው የምረጡኝ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ላይ የተገኙት የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ
ምርጫው የሕዝብ ፈቃድ የሚፈፀምበት ምርጫ እንዲሆን ፓርቲያቸው በንቃት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ በርካታ እድሎች መክነዋል ያሉት ሊቀመንበሩ በርካታ መስዋዕትነት የተከፈለበት እና ተስፋ የተጣለበት
የ2013 ዓ.ም ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኢዜማ በሰከነ የፖለቲካ መንፈስ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ውስጥ ጉልህ አበርክቶ ያላቸው ሴቶች በ2013 ዓ.ም ምርጫ ንቁ
ተሳትፎ እንዲኖራቸው ኢዜማ እየሠራ መሆኑን ደግሞ በባሕር ዳር ምርጫ ወረዳ የሴቶች ተጠሪ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሳባ
ተዘራ ገልጸዋል፡፡ በየትኛውም የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሴቶች በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለመብታቸው መከበር በንቃት
ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢዜማ ባሕር ዳር እና አካባቢው የምርጫ ወረዳ አስተባባሪ አቶ ካሳየ ሰይድ ምርጫው የሀገሪቱን መፃዒ እጣ ፋንታ ዘዋሪ
መሆኑን ጠቁመው መራጮች የምርጫ ካርድ በማውጣት እና በንቃት በመሳተፍ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ማረጋገጥ
እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በ2013 ዓ.ም ምርጫ በ448 የምርጫ ወረዳዎች የሚወዳደር ሲሆን በአማራ
ክልል በሁሉም የምርጫ ወረዳዎች እጩዎችን መልምሎ እንደሚያወዳድር ከፓርቲው የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
‹‹ንቁ ዜጋ፤ ምቹ ሀገር›› በሚል መሪ ሃሳብ የምረጡኝ ቅስቀሳውን በባሕር ዳር እና አካባቢዋ ዛሬ በይፋ ሲጀምር የፓርቲው
ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አንዷለም አራጌ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ናትናኤል ፈለቀን ጨምሮ
የፓርቲው የሥራ ኀላፊዎች እና ደጋፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
