“የዋጋ ንረቱ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል” ሸማቾች

464

“የዋጋ ንረቱ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል” ሸማቾች

ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን ጠብቀው የማይሰሩት ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

በጤነኛ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ (የምጣኔ ሀብት) እንቅስቃሴ ሂደት ሸማቶች የሚገዙትን ምርት መጠን፣ ጥራትና ምንነት በትክክል ተረድተው በሚያዋጣቸው የዋጋ ተመን ግብይት መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን የማግኘት ህጋዊ መብትም አላቸው፡፡ ነጋዴዎች ደግሞ ህጋዊ ተመን የተቀመጠለት፣ በጥራትም ገበያ ላይ ካሉት ተመሳሳይ ምርቶች ተሽሎ ማሸነፍ የሚችል ምርት በተገቢው ጊዜ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ የገበያ ስርዓት ውስጥ የሚገቡ አምራቾችም ገበያውን ሊመጥን የሚችል በቂ ምርት በማምረት አጠቃላይ ወጫቸውን ሊተካ የሚችል ጥቅም ሊያገኙ ይገባዋል፡፡

Image may contain: 2 people, food and outdoor

በሻጭ እና በገዢ መካከል ያለው ምህዋር እንዳይዛነፍ በመጠንም፣ በጥራትም፣ በጊዜም ተወዳዳሪ የምርት አቅርቦት እንዲኖር መስራት እንደሚጠበቅ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ መስተጋብሩ ጤናማ እንዲሆን ደግሞ መንግስት ኃላፊነት የሰጣቸው አካላት ሚና ጉልህ መሆን እንዳለበት እሙን ነው፡፡ በሀገሪቱ ንግድ ሂደት ዙሪያ የሸማቾች መብትና ግዴታን አስመልክቶ የወጣው የግብይት አዋጅ (813/2006) ይህን ሀሳብ የሚያጠናክር ሆኖ ተደንግጓል፤ ነገር ግን ይህ እየተተገበረ አይደለም፡፡

በአማራ ክልል ተዘዋውረን ያደረግነው ምልከታም ይሁን ከነዋሪዎች የሰበሰብናቸው መረጃዎች የሚያሳዩት የኑሮ ውድነቱ የአብዛኛውን ሕዝብ የመኖር ህልውና እየተፈታተነ መሆኑን ነው፡፡ በተለይ በመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ ያለው ግብይት ሥርዓት የለሽ እየሆነ ይገኛል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎቹን ወይዘሮ ጥሩ ውቤ እና ወይዘሮ ትሁን አስናቀ በባሕር ዳር ትልቁ ገበያ ውስጥ ነው ያገኘናቸው፡፡ ወይዘሮ ጥሩ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ድንችና መሰል የፍጆታ ምርቶችን ሲገበዩ፣ ወይዘሮ ትሁን ደግሞ ሲሸጡ ነው ያገኘናቸው፡፡ ሁለቱም በአንድ ጉዳይ ይስማማሉ፤ የዘንድሮው የመሠረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ብልጫ እንዳለው ነው የነገሩን፡፡

ባለፈው ዓመት ለኪሎ 12 ብር የነበረው ቲማቲም አሁን 25 ብር ሆኗል፤ ያለፈው ዓመት አንድ ኪሎ በ60 ብር ሲሸጥ የነበረው ነጭ ሽንኩርት አሁን 2 መቶ ብር ደርሷል፡፡ ለኪሎ 20 ብር ሲሸጥ የነበረው ነጭ ጤፍ አሁን እስከ 32 ብር ዋጋ ተቆርጦለታል፡፡ ማካሮኒ፣ ፓስታ እና ዘይትም የዋጋ ንረት አሳይተዋል፡፡

Image may contain: food

በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ነዋሪው አቶ ማሬ በሪሁንና በደብረ ብርሃን ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪዋ ወይዘሮ ዓይናለም ተሾመ የዋጋ ግሽበቱ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ እንደሚገኝ ነው ለአብመድ የተናገሩት፡፡

ነጋዴው አድማ በሚመስል የግብይት ሂደት የተመን ዋጋ በአንድነት መክሮ ሲሸጥ ሃይ ባይ የለውም፡፡ የጥራጥሬ፣ የብርዕ እና የአገዳ እንዲሁም የቅባት እህሎችን ጨምሮ መሠረታዊ የግብርና ምርቶችንም ሆነ እንደ ፓስታና ማካሮኒ አይነት የፋብሪካ ውጤቶችን የምርት አቅርቦት እጦት ያለ ለማስመሰል ሲከዘን ተቆጣጣሪ የለውም፡፡ ደባቂዎች ተጠያቂ አይሆኑም፡፡ ጥራት የለሽ ምርቱን ዋጋ ቆልሎ ገበያ ሲወጣም ገዥ አያጣም፡፡ አንዳንድ ጊዜም ምርቱን ሳይሆን ግርዱን ለገበያ ያቀርበዋል፡፡ ኪሎውን ቀሽቦ ሲሸጥ፣ ኪሎ ወይም ግራም በማይሞላ መለኪያ ሲመዝን፣ መስፈሪያውን ቀጥቅጦ መጠኑን ሲቀንስ አማራጭ የሌለው ሸማች ነጋዴው ባስቀመጠው ዋጋ ይሸምታል፡፡

በዚህ የጥድፊያ ግብይት ሂደት እንኳንስ ተከራክሮ ዋጋ ለማስቀነስ ይቅርና አንዱ ሊገዛው በመነጋገር ላይ ያለውን እኔ ጨምሬ እገዛዋለሁ የሚለው ሸማች ቁጥር እተበራከተ እንደሚገኝ ነው ሸማቾች ያስረዱት፡፡ በመሆኑም ቅቤ ብሎ ሙዙን፣ በርበሬ ብሎ አፈሩን፣ እህሉን ብሎ ሳጋቱራውን የሚሸምተው ሸማች ቁጥር እተበራከተ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የዋጋ ንረቱን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግስት አካላት ዳር ተመልካች መሆን የችግሩን መጠን እንዳባባሰው ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት፡፡

Image may contain: 1 person

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በበኩሉ የዋጋ ንረቱ እየተስተዋለ ያለው የሸማቾች ጥበቃ፣ የንግድ አዋጁና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማስከበር እየተደረገ ያለው ጥረት ዝቅተኛ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡ በቢሮው የሸማቾች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ሙሃባው ሙላት እንደተናገሩት ቢሮው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ቢሆንም ህገ ወጦችን በመከላከል የህግ የበላይነትን ማስፈን አልቻለም፡፡ ዘርፉ የብዙ አጋር አካላትን የጋራ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑ ደግሞ ህግ የማስከበር ፈተናውን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል ከፍትህ፣ ከፖሊስ፣ ከማኅበራት … የተውጣጣ ኮሚቴ ቢኖርም ከይስሙላ ባለፈ የሕዝቡን እሮሮ የሚሰማ ተግባር እያከናወነ አይደለም፡፡

ህጋዊዎቹን የሚያበረታታ፣ ህገ ወጦችን ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋትም አልተቻለም፡፡ ቢሮው ከአንድ ወቅት የዘመቻ ሥራ ያለፈ ተግባር እያከናወነ እንዳልሆነም በግምገማ መረጋገጡን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በአምራቾችና በተጠቃሚዎች መካከል ያለው የገበያ ትስስር መላላት፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ተስፋ የተጣለባቸው ኅብረት ሥራ ማኅበራት አቅም መዳከም ሌላኛዎቹ የዘርፉ ፈተናዎች እንደሆኑም አቶ ሙሃባው ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በተደረገ ቅኝት ከ18 ሺህ በላይ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች ህጉን ጠብቀው አለመስራታቸው ተረጋግጧል፡፡ ከነዚህ መካከል 17 ሺህ 966ቱ ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብሏል ቢሮው፡፡

ይህንን አጠናክሮ በመቀጠል በተያዘው በጀት ዓመትም ቢሮው ችግሮቹን ለይቶ የዋጋ ንረትን በመቀነስ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ ሙሃባው ያስረዱት፡፡

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

Previous articleየአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ የ2012 አዲስ ዓመት ዋዜማ ልዩ ዝግጅት መልዕክት
Next articleየአማራ ሕዝብ በ2012 በአንድነት በመቆም ድህነትንና የህልውና ፈተናዎችን የሚወጣበት እንደሚሆን ተገለጸ፡፡