
በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚኖር የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግድያና መፈናቀል ሊቆም እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዙር ስድስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬም እየተካሄደ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላትም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የአማራ ሕዝብ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት በማንነቱ አንገቱን እንዲደፋ፣ እንዲገደል እና እንዲፈናቀል የተፈረደበት የአማራ ሕዝብ አሁንም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሞት ታውጆበታል ብለዋል የምክር ቤቱ አባላት፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ በጽናት በማመኑ ሕልውናው አደጋ ላይ ወድቋልም ብለዋል፡፡ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግድያና መፈናቀልም ሊቆም እንደሚገባ የምክር ቤት አባላቱ ጠይቀዋል፡፡
ይህንን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንዲረዱት መሥራት ይገባል፤ መላው ኢትዮጵያውያንም የአማራ ሕዝብን ሊታደገው እንደሚገባ ነው የምክር ቤቱ አባላት የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳር አገኘሁ ተሻገር ማንነትን መሠረት አድርጎ እየደረሰ ያለው ግፍና ሰቆቃ ከዚህ በላይ እንዳይሆን መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ይህም የ27 ዓመታት የአማራ ሕዝብ ጠላት የሆኑ ቡድኖች ያዘጋጁት ወጥመድ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ምንም እንኳን ፈተናውን ለማለፍ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም አሁንም ከፍተኛ ትግል እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡ በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ እንዲቆም መፍትሔው ተጨባጭ ትግል ማድረግ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያለ አመራር ለመታገል ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡
በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሕዝብ ትስስር እንዲጠነክር መስራትም የችግሩ መፍትሔ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሕዝቦች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ በደንብ መነጋገር አስፈላጊ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ ለዚህም ከክልሎች ጋር የሚኖር ግንኙነትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ ጉዳይ ራሱን የቻለ አጀንዳ ይዞ በፌዴራል ደረጃ መነጋገር እንደሚያስፈልግም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ሕዝብም ሊያዳምጠን ይገባል” ብለዋል አቶ አገኘሁ፡፡
በሌላ በኩል በአማራ ክልል ውስጥ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳይገጥም የክልሉን አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ይገባል ነው ያሉት፡፡ ክልሉን ለማተራመስ የሚፈልጉ ኀይሎች መኖራቸውን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ በንቃት መከታተል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
