በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ክትባት በባሕርዳር ከተማ ፈለገህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዛሬ መሰጠት ተጀምሯል፡፡

228
በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ክትባት በባሕርዳር ከተማ ፈለገህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዛሬ መሰጠት ተጀምሯል፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በባሕርዳር ከተማ ፈለገህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዛሬ የተጀመረውን የኮሮናቫይረስ ክትባት ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ፣ የጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች አስጀምረውታል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አገኘሁ ተሻገር ወረርሽኙ በአማራ ክልል በተከሰተበት ወቅት የጤና ባለሙያዎች ራሳቸዉን ለአደጋ አጋልጠው፣ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ነገር ግን ሕዝብን ለማዳን ያደረጉት ርብርብ ምንግዜም በታሪክ የሚረሳ ተግባር አይደለም ብለዋል። ራስን ለሕዝብ አሳልፎ ለመስጠት ሲባል በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች በወረርሽኙ ሕይወታቸውን እንዳጡ ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ሁሌም ሲያስታውሳቸው ይኖራል ብለዋል።
ክትባቱ የሚሰጠውም ተጋላጭ ለሆኑ የጤና ባለሙያዎች፣ እድሜያቸው ከ65 በላይ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው ዜጎችና በየደረጃው ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚዳረስ ይሆናል ብለዋል። “የወረርሽኙ መከላከያ ክትባት ዛሬ በባሕር ዳር በይፋ በመጀመሩ መላው ሕዝባችን እንኳን ደሥ አላችሁ” ብለዋል አቶ አገኘሁ በንግግራቸው።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ባደረጉት ንግግር ክትባቱ ወረርሽኙን ፊትለፊት ለሚጋፈጡ ለጤና ባለሙያዎች፣ እድሜያቸው 65 በላይ ለሆኑ ዜጎች ቅድሚያ የሚሠጥ እንደሆነና በሂደት የጤና ሚኒስቴር በሚኖረው አቅምና ባሳወቃቸው ልክ እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ይዳረሳል ብለዋል።
ዶክተር መልካሙ በንግግራቸው “ክትባቱ የወረርሽኙን መከላከል ሊተካ ስለማይችል፣ የቅድመ መከላከል መርሆዎችን ክትባቱ መጥቷል በሚል ሀሳብ መዘንጋት አያስፈልግም” በማለት አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ 108 ሺህ ዶዝ ክትባት በየደረጃው ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። በክልሉ 251 ሺህ 871 ሰዎች ተመርምረው 7 ሺህ 431 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው አስረድተዋል።
6 ሺህ 867 ሰዎች ከበሽታው እንዳገገሙና 140 ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ አማካኝነት ሕይወታቸውን ማጣታቸዉን አቶ በላይ አብራርተዋል። አቶ በላይ ኅብረተሰቡ ሲያደርግ የነበረዉን የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት መቀጠል አለበት ብለዋል።
የፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል በነርስነት ሙያ እያገለገሉ የሚገኙት ሲስተር መዓዛ ላመስግን የኮሮናቫይረስ ክትባትን የወሰዱ ሰዎች ከሁለት ወራት በኋላ ሁለተኛዉን ክትባት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ክትባቱ ወረርሽኙን 63 ነጥብ 1 በመቶ ሊከላከል እንደሚችል ባለሙያዋ አስረድተዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት የማስጀመሪያ መርሃግብር ዛሬ በመላ ሀገሪቱ ተካሂዷል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሀገር ሞተ የሚባለው አንድ ሰዉ ሲሞት፤ ሀገር ለማ የሚባለውም አንድ ሰው መልማት ሲጀምር መሆኑን ለዘነጉ የሥራ ኀላፊዎች ማስታወስ ያስፈልጋል” የአዲስ አበባ አማራ ወጣቶች መኅበር ፕሬዝዳንት
Next articleበተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚኖር የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግድያና መፈናቀል ሊቆም እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት ጠየቁ፡፡