“በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ሁሉም ዞኖች የራሳቸው የሬዲዮ ማሰራጫ እንዲኖራቸው ታቅዶ እየተሠራ ነው” የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሰጥየ

238

“በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ሁሉም ዞኖች የራሳቸው የሬዲዮ ማሰራጫ እንዲኖራቸው ታቅዶ እየተሠራ ነው” የአማራ ብዙኃን
መገናኛ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሰጥየ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የ2012 በጀት ዓመት እና የ2013 በጀት
ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመትን የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት የድርጅቱ ዋና ሥራ
አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ ድርጅቱ ሙያዊ መርህን በመከተል በከፍተኛ ጥራት፣ በወቅታዊነትና በቀዳሚነትና በተደራሽነት
የዘገባ ሥራ ሠርቷል ብለዋል፡፡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ዘገባዎችን ለታዳሚያን ማድረሱንም አስታውቀዋል፡፡
በአንድ ዓመት ከመንፈቅ በአማራ ክልል ብሎም በሀገሪቱ ሠላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ የሕብረተሰቡ
የመከባበርና የመተሳሰብ ባሕል እና የሀሳብ ነጻነት እንዲጎለብት በትኩረት ተሠርቷልም ብለዋል፡፡ የላቀ የብዙኃን መገናኛ
አገልግሎት በመስጠት የሕዝብ እርካታና አመኔታ ለማግኘት ሳቢና ማራኪ የዘገባ ሥራ እንዲኖር ተደርጓል፤ ለዚህም የሠራተኞችን
እና የድርጅቱን የሥራ ኀላፊዎች አቅም መገንባት የሚያችል ስልጠና መሰጠቱን አመላክተዋል፡፡
የድርጅቱን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ እንዲሁም የንብረት አያያዝና አጠቃቀምን ለማዘመንም ተሠርቷል፤ በሁሉም ጣቢያዎች የዘገባ
ቅርጽና አቀራረብን ለማሳደግ በእቅድ መሠራቱንም አስታውቀዋል፡፡
የድርጅቱ ሠራተኞች ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያጋጠሙ ፈታኝ ጊዜያትን ኀላፊነት በተሞላበት የሥራ ቁርጠኝነት ጥራት ዘገባ
መሥራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ተፈጥሯዊና ሠው ሠራሽ አደጋዎች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች
ጭምር ስምሪት ተወስዶ ተሠርቷል፡፡ በተለይ ትህነግ በመከላከያ ሠራዊትና በአማራ ሕዝብ ላይ የጥቃት ሙከራ ማድረጉን
ተከትሎ በተወሰደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በሁሉም ግንባሮች ስምሪት ወስዶ ሠርቷል ብለዋል፡፡
በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ተደራሽነት እና የዘገባ ጥራት እንዲጨምርም በአምስት የተለያዩ ቋንቋዎች ደንበኞችን ማፍራት
የሚያስችል የዘገባ ሥራ ተሠርቷል፡፡ አዲስ አበባ ያለውን ሕዝብ ለማገልገልና የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ዕሴት
ለማስተዋወቅም የአዲስ አበባ የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ጀምሯል፤ የሬዲያ ጣቢያ ቀጥታ ስርጭት ለማስጀመር ዝግጅት
የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ ለማስጀመርም እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የደብረማርቆስን እና የጎንደር ኤፍ ኤም ጣቢያዎችን ግንባታ በማጠናቀቅ ሥርጭት ማስጀመር እንደተቻለም አንስተዋል፡፡
የዋግኽምራ ኤፍ ኤም ጣቢያ ግንባታም በዚህ ዓመት ይጀምራል፤ ለዚህም ትራንስሚተር ተገዝቷል ብለዋል፡፡ ተደራሽነትን
ለማስፋትም አዳዲስ የመረጃ ማሰራጫ አማራጮችን ለማሳደግ ነው እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት አካባቢያዊ ተደራሽነት ካለፉት ዓመታት የተሻለ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ነጻ በወጡ አካባቢዎች
የስርጭት አድማስን ከማስፋት ባለፈ የተለያዩ ወቅታዊ ዘገባዎችን እና ዘጋቢ ፕሮግራሞችን (ዶክመንታሪ) በመሥራት የሕዝቡ
በደል እንዲታወቅ አድርጓል፤ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በመተርጎም ጭምር ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ግብዓት እንዲሆን ማድረግ
መቻሉን አንስተዋል፡፡
የብሔረሰብ ቋንቋዎች ከፍተኛ ተከታታይ በሚኖራቸው ሰዓት እንዲተላለፉ የማስተካከያ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በተጨማሪም
በቋንቋዎች ሥርጭት እንዲጀምር ሁለተኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተያዘው በጀት ዓመት ለመክፈት ጥረት እየተደረገ መሆኑን
አንስተዋል፡፡
የዘገባ ጥራትና ተደራሽነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የማሻሻልና የማላመድ ሥራም ትኩረት ተሰጥቶታል
ብለዋል አቶ ሙሉቀን ባቀረቡት ሪፖርት፡፡ በተለይ የሞባይል ጋዜጠኝነት ትግበራ መጀመሩ ቀዳሚ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በአንዳንድ ዘገባዎች የዘገባ ጥራት መጓደል፣ በበቂ እውቀት ላይ ተመስርቶ ዘገባ አለመሥራት፣ በሳል እቅድ አለማዘጋጀት፣ ሁሉን
አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የተሸከርካሪ እጥረት መኖር እንዲሁም የዘገባ ርዕሰ ጉዳዮችን በጥልቀት ያለመተንተን ውስንነት
እንዳለ አመላክተዋል፡፡ የጸጥታ ችግር መኖር፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሥራ ኀላፊዎች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን
በሥራ ጊዜ ያጋጠሙ ችግሮች እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሉባባ ኢብራሂም
ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ የድርጅቱ ሠራተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ወሳኝ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መሥራታቸውን
ጠቅሰዋል፡፡ አርሶ አደሩ የማኅበረሰብ ክፍል ድረስ በመግባት ወግና ባሕላቸው እንዲተዋወቅ ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡
በተለይ በሕግ ማስከበር ዘመቻው በተለየ መልኩ ታሪክ የማይረሳው የዘገባ ሥራ እንደተሠራም ገልጸዋል፡፡
የዘገባ ሥራዎችን ሳቢና ማራኪ ማድረግ፣ ርዕሰ ጉዳዮችን በስፋትና በጥልቀት መተንተን፣ ከክልሉ ውጪ ወኪል አለመኖር፣
የደብረብርሃን እና የደሴ ቴሌቪዢን ጣቢዎች እንዲሁም የኬሚሴና የዋግኽምራ ኤፍ ኤም ጣቢያዎች ግንባታ መዘግየት
ሊስተካከሉ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ በድርጅቱ የሚስተዋል የተሸከርካሪ እጥረት እንዲፈታም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ በየጊዜው ራሱን እያሳደገ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ
በማድረግ፣ ሀገራዊ ለውጡ በትክክል እንዲመራ እና ሕግ በማስከበር ዘመቻው የተሠሩ ዘገባዎችን በጥሩ አንስተዋል፡፡ ጥራት
ያላቸው ዘጋቢ ፕሮግራሞች (ዶክመንተሪዎች) እየተሠሩ ነው፣ የዘገባ ጥራትም እያደገ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከክልሉ ውጪ
ያሉ አማራዎችን ተደራሽ በማድረግ በኩል ውስንነት እንዳለ ነው ያነሱት፡፡
የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የቴሌቪዥን የዘገባ አቀራረብ አዲስ አሠራር ቢኖረው እና በተለያዬ ሰዓት እንዲተላለፍ ቢደረግ ጥሩ
መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ ያለውን አቅም እያሳደገ መሄድ አለበትም ነው ያሉት፡፡ የሕትመት ሚዲያው
እንዲጠናከርና የውጪ ሀገራት ተደራሽነት እንዲጨምርም ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ሰጥዬ በሰጡት ማብራሪያ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ሁሉም ዞኖች የራሳቸው የሬዲዮ
ማሰራጫ እንዲኖራቸው ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ድርጅቱ በራሱ ወጪ መሳሪያዎችን እየገዛ ቢሆንም ከፍተኛ ወጪ
ስለሚጠይቅ የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጥገና ጥናት፣ ውጤትና ዝርዝር አሠራር ለማኅበረሰቡ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡
Next articleየአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አደገ፡፡