የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጥገና ጥናት፣ ውጤትና ዝርዝር አሠራር ለማኅበረሰቡ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡

135
የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጥገና ጥናት፣ ውጤትና ዝርዝር አሠራር ለማኅበረሰቡ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) በውይይቱ የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸው ተነስቷል፡፡
ቅርሶቹን ከጉዳት ለመታደግ በየዘመናቱ ጥገና የተደረገ ቢሆንም የቅርሶቹን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዝኖ መቆየቱን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱን ከመፍረስ ለመታደግ ማኅበረሰቡ ለተከታታይ ዓመታት መንግሥትን ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡
ከዛሬ 13 ዓመት በፊት ቅርሶቹን ከዝናብና ከፀሐይ ለመታደግ ተብሎ የተሸራው መጠለያም ከሚሰጠው አገልግሎት ይልቅ በቅርሱ ላይ አደጋ ደቅኗል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ወደ ስልጣን ከመጡ ማግስት ጀምሮ በተደጋጋሚ ቅርሱን በመመልከት ችግሩን ለመፍታት ከፈረንሳይ መንግሥት የበጀትና የባለሙያ ድጋፍ እንዲገኝ ስምምነት በመፍጠር ባለፉት ሁለት ዓመታት የጥገና ሥራው አንድ አካል የሆነው ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
ጥናቱን ያጠኑት የፈረንሳይ አርክቴክቶች የጥናቱን ውጤት ለሚመለከታቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በማቅረብ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የላልይበላ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሪጌታ መልካሙ ዓለሙ እንደሚሉት ቅርሱን ለመጠገን በተገባው ቃል መሰረት የጥናት ሥራው ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በቀጣይ ወደ ጥገናው ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ማለትም የስቶር ግንባታ ሥራ፣ የጥገና ማቴሪያሎችን የማስገባት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደሚሉት ደግሞ ቅርሶቹን ጠብቆ ለማቆየትና በአፋጣኝ የቅርስ ጥገናውን ለማድረግ የጥናት ውጤቱን ለሚመለከታቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በማቅረብ እንዲወያዩበት እየተደረገ ነው፡፡
የቅርሶቹን ጥገናና የመጠለያ ሥራን በተመለከተ በጥናት የተገኘውን የመፍትሄ ሃሳብ እና የአሠራር ቅደም ተከተሉን ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠርም እንደሚሠራ መግለጻቸውን ከላልይበላ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየ2013 ዓ.ም የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ ከ50 በመቶ በላይ መጠናቀቁን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next article“በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ሁሉም ዞኖች የራሳቸው የሬዲዮ ማሰራጫ እንዲኖራቸው ታቅዶ እየተሠራ ነው” የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሰጥየ