
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ የ2012 አዲስ ዓመት ዋዜማ ልዩ ዝግጅት መልዕክት
ሙሉ መልዕክቱን ያንብቡት
የተከበራችሁ የአማራ ክልል ህዝቦች፤
የተከበራችሁ መላው የአገራችን ህዝቦች፤
ክቡራን የሃይማኖት አባቶች፤
የተከበራችሁ የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች፤
የተከበራችሁ የዞን፣ የከተማ፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች፤
ክቡራን የባህር ዳር ነዋሪዎች፤
ክቡራን ጥሪ የተደረገላችሁ ምሁራንና ባለሃብቶች
ክቡራትና ክቡራን
በቅድሚያ ሁላችንንም እንኳን ከዘመን ዘመን በሰላም አሸጋገረን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት፤ እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ፡፡ በዚህ አይነቱ ለየት ባለ ሁኔታ በተዘጋጀ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ዝግጅት ተገኝቼ መልዕክት ማስተላለፍ በመቻሌ የተሰማኝ ደስታ እጥፍ ድርብ መሆኑን እየገለፅኩ ‹‹ማቅ አውልቀን፤ ግምጃ እንልበስ›› በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው በዚህ የዋዜማ ክብረ በዓል ላይ ጥሪ ስናስተላልፍላችሁ ፈቅዳችሁ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ክብረ በዓላችን ተካፋይ ለመሆን በመምጣታችሁ በክልሉ መንግስት፣ በህዝቡና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን እያቀረብኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ወደ ሆነችው ውቢቷ ከተማችን ባህር ዳር እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
ክቡራትና ክቡራን፡-
ኢትዮጵያ የፍጥረታት ሁሉ መነሻ ምድረ ቀደምት፣ የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት፣ የገናና ስልጣኔ አምባ፣ የአኩሪ ተጋድሎ እና ድል ባለቤት ሀገር ስትሆን ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የኩራት ምንጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የኩራት ምንጭ ነው ስንል ሀገሪቱ ጥንታዊነት እና የገናና ስልጣኔ ባለቤት የነበረች መሆኑ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ውብ ባህሎች ሀገር በመሆኗም ጭምር ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ባሕሎች ዘርፈ ብዙ እና ውቦች ናቸው፡፡ ከባሕላችን መገለጫዎች መካከል አንዱ የበዓል አከባበር ስርዓታችን ነው፡፡ በዓላት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ቦታና ትርጉም አላቸው፡፡ በተለያዩ በዓላቶቻችን እንደ ሕዝብ ትዝታችን ተጽፎባቸዋል፤ ህብረታችን ታትሞባቸዋል፣ ማህበራዊ ትስስራችን ተገምዶባቸዋል፤ ተስፋችን ተበስሮባቸዋል፡፡ የዘመን መለወጥን ማብሰሪያው የአዲስ ዓመት በዓልም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በጋራ የምናከብረው፤ ከከረምንበት ጭጋጋማ ብርዳማ ክረምት፣ ተስፋን ወደምትፈነጥቀው የጸደይ ፀሀይ፤ ማብሰሪያ ወቅት የሚከበር በመሆኑ፤ ልዩ ስሜት ይሰጣል፤ ለዚህም ነው ብዙዎቻችን የአዲስ ዓመት በዓል ትዝታ የሚናፍቀን፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ የተገነባችበት ሁኔታ፤ እንደ ታሪኳ ሁሉ ረዥም ጊዜ የፈጀ፣ በጥልቅ ጥበብ የተበጀ ነው፡፡ ይህቺ ድንቅ አገር የተገነባችው በቅድመ አያቶቻችን ብርቱ ታታሪነት፣ደም እና አጥንት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር እና ክብሯን ለማስጠበቅም፤ የአማራ ክልል ሕዝቦች ከሌሎች እህት እና ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ሳይሰስቱ ፊት ለፊት ግንባራቸውን ሰጥተዋል፡፡ ለዚህም ቅዱስ ተግባራቸው ለዘላለም ስናከብራቸው፣ ስናመሰግናቸው እና ስንመካባቸው እንኖራለን፡፡
ዓለም የሚመሰክረው እኛም የምናውቀው ሀቅ የአማራ ክልል ሕዝቦች መነሻ እና መድረሻቸው፤ የኢትዮጵያ ጥንካሬ እና ታላቅነት ነው፡፡ ይህም ዕውን የሚሆነው፤ በሁሉም የኢትዮጵያውያን ሕብር እና እኩልነት እንደሆነ በጽኑ ያምናሉ፡፡ የአማራ ክልል ሕዝቦች፤ በኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ፈተናዎችን አልፈዋል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የፈለገ ጠላት ሁሉ፤ የመጀመሪያ ኢላማ አድርጎ ግፍና መከራ የሚያደርስበት፣ ባህሉን ለማጥፋት የሚረባረብበት፤ ወጉን ለማኮስመን የሚታትርበት የአማራ ክልል ሕዝቦችን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ የሆነበት አበይት ምክንያ የአማራ ክልል ሕዝቦች ለኢትዮጵያ እና ለህብረ ኢትዮጵያዊነት ቀናኢ በመሆናቸው ነው፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለመካድና ለመርሳት ወይንም ለመጥራት እና በውስጣቸው ለመኖር መስጋት፤መጠራጠር፤ መዘንጋት ለሚሹ አካላት ከላይ የጠቀስኳቸውን የኩራት ምንጮች የሆኑ ውብ የአባቶቻችን ባህል፣ ወግ፣ ወኔና ጀግንነት አለማወቅ፤ ወይንም እያወቁ ሆነ ብሎ ማጥፋት በመሆኑ የእንዲህ አይነት አባዜ የተጠናወታቸው አካላት ሁሉ፤ በአዲሱ ዓመት ፈጣሪ ቅን ልቦና እንዲሰጣቸው እንመኛላቸዋለን፡፡
ክቡራንና ክቡራት፡-
ባለፉት በርካታ ዓመታት በመጣንበት ጉዞ ውስጥ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና ሳንካዎች እጅግ ብዙ እና ውስብስብ ቢሆኑም ከፊሉን ተገዳድረን እያለፍን ብዙውን ግን በአሸናፊነት እየተወጣን እዚህ ደርሰናል፡፡ በየጊዜው ያጋጠሙንን ፈተናዎች እንዴት ማለፍ እንደቻልን ልምድ እና ተሞክሮ ያለን ህዝቦች ስለሆን፤ ባለፉት ጊዜያት በአገራችን በተለይም በክልላችን ያጋጠሙንን ፈተናዎችም፤ በአሸናፊነት መወጣት ጀምረናል፡፡ ችግር ሲያጋጥመን እንዴት መፍታት እንዳለብን የተማርነው፤ ከቀደምት አባቶቻችን ነው፡፡ እኛ የጠበብት አባቶች ልጆች ነን፡፡ አይደለም በጥንታዊቷ ይቅርና በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንኳ የኢትዮጵያንም ሆነ የአማራን ሕዝብ በእጅጉ ህልውናውን የሚፈታተኑ፣ አያሌ ጉድጓዶች ተምሰዋል፡፡ ይሁንና፤ በፈተና ወቅት ወደ ኋላ መንደርደር ማለት ለባለ ራዕይ ወደ ፊት እንዴት እንደሚያስወነጭፍ አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ እኛም የአባቶቻችን ልጆች ነንና፤ ዛሬም ብዙ የችግር አረንቋዎች አልፈን እዚህ ደርሰናል፡፡ አበው እንደሚሉት ችግር ሲገጥመው የሚደነግጥ ከዚህ ቀደም ያለ ችግር የኖረ ሰው ነው፡፡ በብዙ ችግር ያለፈ ሰው ግን የሚያጋጥመውን ፈተና በብቃትና በአሸናፊነት ይወጣዋል፡፡ እኛም እንደ ሕዝብ የብዙ ተግዳሮቶች ውል የሚፈታበትን ጥበብ የያዝን ስለሆነ ባለፈው ጊዜ በክልላችነ አጋጥሞን የነበረውን አስጨናቂና ከባድ ጊዜ ተቋቁመን ይኸው እዚህ ደርሳል፡፡ ይህ ክስተት ያደረሰብን የህይወት የንብረትና የስነ ልቡና ጉዳት ከባድ ቢሆንም በደረሰብን ሀዘን እየቆዘምን እንደ ዶሮ አንገት ደፍተን መሬት ስንጭር የምኖር ደካሞች አይደለንም፡፡
ክቡራንና ክቡራት፡-
አጋጥሞን የነበረው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ቢያስገባንም ለሕዝባችን ስንል ከሀዘን ቶሎ መውጣት ነበረብን፡፡ ሀዘን ማብዛት ትረፉ የበለጠ ለችግር መጋለጥ ነው፡፡ መሪ በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሀዘን ጊዜም ጭምር ሕዝቡን እየመራ ማሻገር አለበት፡፡ በሀዘን በመቆዘም የምናተርፈው ነገር የለም፡፡ የሚሻለን የወንድሞቻችንን ህልም እውን ማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ያጋጠመን ጉዳት ወደ ባሰ ችግር ሳይሸጋገር ከሕዝባችን ጋር ሆነን በጥበብ በመወጣት ከማቅ ወደ ግምጃ ከምንሻገርበት ቀን ደርሰን፤ ይኸው ዛሬ በእናንተ ፊት ግምጃ ለብሰን መቆም ችለናል፡፡
የማያሳፍረንና የማያሳንሰን የክልላችን ሕዝብ፤ ከጎናችን ሁኖ ስለደገፈን በሕዝባችን አይዞህታ ተረጋግተንና ተበረታተን፤ ይኸው ዛሬ ማቅ አውልቀን ግምጃ ለብሰን ለተጨማሪ ተስፋ እና ድል ወደ መጪው ብሩህ ዓመት እንሸጋገር ዘንድ ቆርጠን ተነስተናል፤ አዲሱን ዓመት ስንቀበል ከሕዝባችን ጋር ጣትና ጥፍር ብቻ ሳይሆን ደምና የደም ስር ሆነን የምናከናውናቸውና ውጤት የምናስመዘግብባቸው በርካታ ተግባራት ሰንቀናል፡፡ በአዲሱ ዓመት “ማቅ አውልቀን ግምጃ እንለብሳለን” ስንል ከመቼውም ጊዜ በላቀ መንገድ ለሁለንተናዊ ልማትና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንሰራለን ማለታችን ነው፡፡
በመሆኑም በመጪው ዓመት የተስፋ ግምጃችንን ለመልበስ ጠንካራ የመንግስትና የፓርቲ አደረጃጀትና ተቋማዊነት እንፈጥራለን፡፡ ህግን የማስከበርና የሕዝብን ደህንነት ዋስትና የሚሰጥ የፀጥታ እና ፍትህ መዋቅሮችን ተደራሽና ጠንካራ እናደርጋለን፡፡ ለዘመናት ስር ሰዶ ያለውን ድህነት የመቀነስ ትግል አጠናክረን የልማትና የኢንቨስትመንት ተግባራትን ከምንጊዜም በተሻለ ቁርጠኝነት ለማሳካት እንረባረባለን፤ ግብርና ትልቁ የትኩረት ማዕከላችን ይሆናል፤ የሥራ ዕድል ፈጠራ በሁሉም ዘርፎች በተለይም ደግሞ በግብርና ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም ዘርፎች በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፤ በመጪው ዓመት ክልላችንን ብቻ ሳይሆን ሀገራችንንም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው ፋብሪካዎችን ስራ ለማስጀመር ጥረት ይደረጋል፤ በእነዚህም ትርጉም ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እንቀሳቀሳለን፡፡ ከክልል ውጭ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ሁለንተናዊ መብታቸው እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራና በትብብር እንሠራለን፡፡ በአገራችንና መላው ዓለም ከሚገኙ ምሁራን ባለሀብቶችና ከመላው ሕዝብ ጋር በመቀራረብና በመመካከር የልማት የሰላምና የዴሞክራሲ ትግላችንን በትብብር ለመሥራት ከምንጊዜውም በላይ እንተጋለን፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች የሕዝባችንን ደህንነት እና ሕገ መንግስታዊ መብት በሚያረጋግጥ ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ የሕዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና አገራዊ አንድነት ለመፍጠር እየተሠራ ነው፡፡
ክቡራትና ክቡራን፡-
በዚህ ልዩ የዋዜማ ዝግጅት በሀዘናችን ወቅት ከጎናችን ለነበሩ ሁሉ ምስጋናና በእግረ መንገዱም አደራ አቀርብ ዘንድ እንድትፈቅዱልኝ እጠይቃለሁ፤
እናንት የእውነተኛ ህብረ መገለጫ የሆናችሁ የአማራ፣ የአገው፣ የኦሮሞ፣ የአርጎባ፣ የቅማንት በጥቅሉ የክልላችን ሕዝቦች፣ በተለይም ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በዚያ የማቅ ወቅት ከጎናችን ባትሆኑ ኖሩ ዛሬ ለዚህ ግምጃ አንደርስም ነበር፡፡ ለአስተዋይነታችሁና ለአርቆ ተመላካችነታችሁ ክብር ይገባችኋልና የክልሉ መንግሥት በእጅጉ ያመስግናል፡፡ እናንተን ይዘን የማናሳካው እቅድ አይኖረንም፡፡ በመሆኑም መላው የክልላችን ሕዝቦች ከክልሉ ወጪና በተለያየ የዓለም አካባቢ የምትኖሩ ወገኖቻችን እኛ ህልማችን በሁለንተናዊ መልኩ የለማና ያደገ ሕዝብና ከባቢ መፍጠር ነውና፤ ለዚህ እውን መሆን ከመቼውም በላይ ቆርጠን እንደተነሳን አውቃችሁ ከጎናችን በመሆን እንድታግዙን ስንደክም እንድታበረቱን ስንሳሳት እንድታርሙን በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ እናንተ የዕምነት ተቋማት የሃይማኖት አባቶች፤ የአገር ሽማግሌዎች ያለ እናንተ ተግሳፅና ምክር፤ ያለ እናንተ ቡራኬና ፀሎት፤ እንዲሁም ያለ እናንተ ግልግልና እርቅ አገር አይረጋም፡፡ በሃገራችን ያሉ ሁሉንም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ስንመረምረው ሁሉም ሰላምን፣ ፍቅርን፣ መቻቻልን፣ መተባበርንና አንድነትን የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ የኛ ህዝብ እንኳን የሰው ሊወስድ የወደቀ ቢያገኝም አንስቶ ለባለቤቱ የሚሰጥ፣ ጠብ ቢያጋጥመው በህግ አምላክ የሚል፣ እንግዳ ቢመጣበት እግር አጥቦና ከአልጋው ወርዶ የሚያስተናግድ፣ ምን ይሉኝ የሚገደው ሆኖ የዘለቀው በእናንተ አስተምህሮ ነው፡፡
በተለይም የክርስትናም ይሁን የእስልምና አስተምህሮት በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትውልድን በጥሩ ስነ ምግባር በመኮትኮትና በማሳደግ ፊደል ቀርፆና ብራና ፍቆ አሁን ለደረስንበት ዘመናዊ ትምህርት መሰረት የጣለ ሃገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜ በገጠማት የውጭ ወረራም ይሁን የውስጥ ችግሮች ለሃይማኖታቸውና ለሃገራቸው ክብር ሲሉ ክርስቲያኖች መስቀላቸውን፣ ሙስሊሞች ኪታባቸውን ይዘው ተፋልመዋል፡፡ አኩሪ መስዋዕትነትና ገድል ፈፅመዋል፡፡ በመሆኑም ሃገራቸውንና ሃይማኖታቸውን ለዚህ ትውልድ አስረክበዋል፡፡ ይህ ሃይማኖትንና ሃገርን የመከፋፈል ጥቃት በተለያዩ ጊዜያት በውስጥም ይሁን በውጭ ሴራ ተሞክሮ የከሸፈና ያልተሳካ የደካሞች እኩይ ዕቅድና ድርጊት ነው፡፡ ባሳለፍነው ወርም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቃጣው ሃይማኖትን የመከፋፈል ሴራ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እና መንግስት ከእምነቱ ተከታዮችና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን በጋራ ልንመክተው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ባሳለፍነው ከባድ ወቅትም በፀሎትና በምክር ከጎናችን እንዳልተለያችሁን ሁሉ መጭው ዘመን ያሰብነውን የምንተገብርበት ይሆንልን ዘንድ ፀሎታችሁ፣ ምክራችሁ፣ አይዞህ ባይነታችሁ እንዳይለየን፣ በትህትናና በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
የክልላችን ሆነ የአገራችን የዛሬም ሆነ የነገ ተስፋ የሆናችሁ ወጣቶቻችን፣ እኛ ከእናንተ የምንፈልገው ነገር እንዳለ ሁሉ፣ እናንተም ከእኛ ብዙ ነገር እንደምትፈልጉ እናውቃለን፡፡ የእናንተ ፍላጎት አቅም በፈቀደ መጠን ለሟሟላት፣ ሌት ከቀን እየሰራን እንደሆነ አውቃችሁ፣ ለእቅዶቻችን ስኬት ግንባር ቀደም ሆናችሁ ተሰለፉ እኛንም ደግፉን፡፡ ምክንያታዊ ሆናችሁ ሞግቱን እንጂ አታደናቅፉን፡፡ እናንተ ክፍተቶቻችንን ማሳየት አንዳንዱን ደግሞ እናንተም መሙላት ይጠበቅባችኋል፣ ለእናንተ በተለይም ለመላው ህዝባችን ህልውና ብለን፣ ህግና ስርአት ለማስከበር በምንንቀሳቀስበት ጊዜ፣ ለሰላም ስትሉ አግዙን እንጂ አታስተጓጉሉን፡፡ ይልቁንስ ተከባብረን ስለነጋችን በመነጋገር እና በመመካከር የክልላችንን ብሎም የአገራችንን ልዕልና በማስጠበቅ ወደ ተሻለ ምዕራፍ የማሸጋገር ታሪካዊ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ምክሬን እለግሳለሁ፡፡
የክልላችን አርሶ አደሮች፣ በአዲስ አመት አዲስ ተስፋ ሰንቃችሁ፣ አርሳችሁ እና አለስልሳችሁ የዘራችሁት ሰብል መልካም ቡቃያ እያያችሁ፣ በምትገኙበት በዚህ ጥሩ ወቅት ላይ ትገኛላችሁ፡፡ እናንተ ምንጊዜም ከእርሻ ስራችሁ ማንም አይነጥላችሁም፣ ሊነጥላችሁ የሞከረም አልተሳካለትም ፤ አሁንም ይህን ተግባራችሁን አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ እምነቴ የጸና ነው፡፡ በመጪው አመት ግብርናን ለየት ባለ የአሰራር ሁኔታ በሙከራ ደረጃ በአንዳንድ አካባቢዎች ለመጀመር አቅደናል፡፡ ይህ አሰራርም ስኬታማነቱ ከተረጋገጠ ደረጃ በደረጃ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ይረዳል፡፡ በትንሽ መሬት ብዙ ማምረት እና ሰፊ ገቢ ማግኘት የሚያስችል ፕሮጀክት በመሆኑ ለልጆቻችሁም መልካም የስራ እድል አማራጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡
በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ሀብት ላይ ያተኮረ በመሆኑ የአመጋገብ ስርዓታችንንም ለማሻሻል ይረዳናል፤ ሰላማችሁን ነቅታችሁ ጠብቁ፡፡ አዳዲስ የአሰራር ዘዴዎችን ጠቃሚነት ተረድታችሁ ተግብሩ፡፡ የመንግስት ድጋፍ በመጪው አመት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ አደራ የምላችሁ ነገር ትርፍ አምርቱ፤ እናተ እያላችሁ ክንዳችሁ ሳይዝል ኢትዮጵያውያን መራብ የለባቸውም፡፡
እናንት የአማራ ክልል ምሁራን፡- የክልላችንን ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ የምሁራን ሚና የማይተካ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ስለሆነም የክልሉን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እንድትደግፉ ፣ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናት እና ምርምሮችን እየሰራችሁ ፣ሳይማር ያስተማረ ወገናችሁን ወደ ብልጽግና ለማሻገር፣የመፍትሔ አካል ሆናችሁ እንድታገለግሉና የማህበረሰብ አገልግሎት ኃላፊነታችሁን በተግባር እና በቅርበት እንድትወጡ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ፡፡
የክልላችን ባለሀብቶች፣ ዳኞች፣ የፍትህ እና የጸጥታ አካላት፣የመንግስት እና የግል ዘርፍ ሙያተኞች፣የሚዲያ አካላት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ባለጥበቦች፣የማህበረሰብ አንቂዎች፣ተማሪዎች በጥቅሉ ሁላችሁም ወገኖቻችን በየተሰማራችሁበት ሙያ በኃላፊነት መንፈስ ፣ በንጹህ ሰብዕና፣በተቆርቋሪነት እና በቁጭት ለሰላም፣ለዕድገት እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ታገለግሉ ዘንድ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ፡፡ በምታደርጉት ህግ እና ስርዓትን የተከተለ እንቅስቃሴያችሁ ሁሉ ለሚያጋጥማችሁ ተግዳሮት የክልሉ መንግስት በየትኛውም ቦታና ሰዓት ከጎናችሁ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡
ክቡራት እና ክቡራን፡-
የአማራ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በብዛት እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ ተጋብቶ እና ተዋልዶ እንደጠፍር አልጋ ከሁሉም ጋር ተጋምዶ ይኖራል፡፡ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ጥሪ ማቅረብ የምፈልገው ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የአማራ ህዝብ በየአካባቢያችሁ የሚኖረው አንድም ሀገሩ ስለሆነ እንደ ኢትዮጵያዊነቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እናንተ ወንድሞቹ እና እህቶቹ ስለሆናችሁ፣ እንደ ትናንቱ ነገም አብራችሁ ተሳስባችሁ በፍቅር እንደትኖሩ፣ በመካከላችሁ የሚገባውን አሜካላ ጊዜ ሳትሰጡ እንድትነቅሉ እያሳሰብኩ ከእናንተ በላይ ስለእናንተ መስተጋብር የሚያውቅ እና የሚረዳ የሌለ መሆኑን ተረድታችሁ በቆዬው የኢትዮጵያዊነት መንፈስና ስሜት በሰላም እንደትኖሩ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡
ክቡራን እና ክቡራት
እናንት የምወዳችሁ እና የማከብራችሁ የአማራ ክልል ህዝቦች፤ ዛሬ በዚህ ልዩ ‹‹የማቅ ማውለቂያና ግምጃ መልበሻ ቀን›› በአዲሱ አመት የሚኖረኝ የመልዕክት ማሰረጊያ የሚከተለው ነው፡፡ ኑ የተስፋችንን ጥጥ በጋራ እንዳምጠው፣ በአንድነት እናዳውረው፣ በህብረት እንፍተለው፣ በሕብራዊነት እናቅልመው፣ በፍቅር እንሸምነው፣ በያገባኛል ስሜት እንስፋው፣ በባለራዕይነት እንቋጨው፣ ኑ የጋራ የሰላምና እድገት ግምጃችንን በጋራ እንልበሰው፡፡ የእኛ ተስፋ እኛው ራሳችን እንጂ ማንም የሚሰጠን ወይም ማንም የሚነሳን አይደለም፡፡
በመጨረሻም ለዚህ የደመቀ፣ የአማረ እና የተሳካ የበዓለ ዋዜማ የሃሳብ ጠንሳሾች እና በዝግጅቱ ላይ ለተሳተፋችሁ አካላት ሁሉ በክልሉ መንግስት፣ ህዝብና በራሴ ስም ላቅ ያለ መስጋናዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡
በድጋሚ እንኳን ለ2012 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ከመላው ቤተሰቦቻችሁና ወዳጅ ዘመዶቻችሁ ጋር በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን፡፡
መጭው ዘመን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የብልፅግናና የአንድነት ዓመት ይሁንልን!
አመሰግናለሁ