
ባለፉት ስድስት ወራት ከልማት ድርጅቶች ምርትና አገልግሎት ሽያጭ 158 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተሰበሰበ።
ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ባለፉት ስድስት ወራት ከልማት ድርጅቶች ምርትና አገልግሎት ሽያጭ 158 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የፌዴራል መንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
ኤጀንሲው 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማግኘቱንም ገልጿል፡፡
21 የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የሚያስተዳድረው ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ 173 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እንደነበር የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኀይለ ሚካኤል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ፣ በኮሙዩኒኬሽን፣ በፋይናንስ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በግንባታ፣ በማምረትና በንግድ አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የገበያ ክፍተትን የመሙላትና ፖሊሲ የማስፈጸም ሚናቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል፡፡
ድርጅቶቹ ከጠቅላላው የመንግሥት ገቢ 5 በመቶ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ደግሞ 10 በመቶ የሚሸፍኑ እንደሆኑም ኤጀንሲው ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ንግድ ባንክና ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛውን የገቢ ድርሻ እንደሚይዙም ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወር ሥራዎችን የሚያግዙ አሰራሮችን በመዘርጋት አፈጻጸማቸውን እየተከታተለ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የልማት ድርጅቶች የቦርድ መሪዎች ብቃትንና የትምህርት ዝግጅትን መሰረት ተደርጎ እንዲሰየሙ ተደርገዋል ብለዋል፡፡
በዚህም ተቋማቱ ላይ የሚታዩ ለውጦች መጥተዋልም ነው ያሉት፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት፣ ደካማ የፕሮጀክት አስተዳደር፣ የጸጥታ ችግር፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና የውጭ ምንዛሬ ችግሮች ለድርጅቶቹ ሥራዎች ፈተና መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
