
በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በንጹሃን አማራዎች ላይ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በፅኑ አወገዘ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) የመኢአድ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ ይልቃል ደሳለኝ በሰጡት መግለጫ ኦነግ ሸኔ በሚል የሚጠራውና ከኦሮሞ ሕዝብ ባህልና እምነት ፈጽሞ የተቃረነ ሰው በላ ቡድን እና ተባባሪዎቹ የካቲት 27/2013 ዓ.ም ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ እስከ ምሽቱ 3፡20 ድረስ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በአቢ ዳንጎሮ ወረዳ ደቢስ በአለ እግዚአብሔር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እና ሌሎች ሦስት ቀበሌዎች ውስጥ በሚኖሩ ንፁሃን አማራዎች ግድያ ሲፈጸም፤ በርካቶች እገታና ከፍተኛ የሆነ የንብረት ዝርፊያ እንደደረሰባቸው ገልጿል፡፡
ዜጎች ተወልደው ባደጉበት በገዛ ሀገራቸው መጤ እየተባሉ እየተሳደዱና እየተገደሉ መሆኑንም መግለጫው ጠቅሷል፡፡ በየአካባቢው እየተስተዋለ ያለውን ማንነትን መሠረት ያደረገ ዘር ማጥፋትና መፈናቀልን የሚያስቆም የመንግሥት አካል መጥፋቱ ደግሞ እጅግ በጣም አሳሳቢ መሆኑን መኢአድ አስታውቋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ወያኔ በከለለው አጥር ውስጥ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያለማቋረጥ እየታየ ያለው ዘር የማጥፋት ወንጀል መንግሥት ሕዝብን ለመጠበቅ ያጣው አቅም ሳይሆን ፍላጎት ማጣት እንደሆነ መኢአድ ያምናል በዝምታ በማየትም ተጠያቂ ነው ብሏል፡፡ መንግሥትም ሀገርንና የሚያስተዳድረውን ሕዝብ ከአደጋ የመጠበቅና ደኅንነቱን የማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ አለበት ብሏል፡፡
መኢአድ በጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ሁሉ የተሰማውን መሪር ሐዘን ገልጾ፣ በአስቸኳይ ዜጎች መፍትሔ ያገኙ ዘንድ የሚከተሉትን ጥሪዎች አቅርቧል፡፡
1ኛ. መንግሥት በአማራ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ተግባር ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ወስዶ ሕዝቡን ከእልቂት እንዲታደግ
2ኛ. በአራቱም የወለጋ ዞኖች የሚገኙ ወገኖች ላይ በኦነግ ሽኔ አሸባሪ ቡድን አማካኝነት በደረሰው ግድያና መፈናቀል መንግሥት በአስቸኳይ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግና ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እርዳታና ድጋፍ ለማድረግ እንዲረባረቡ፤
3ኛ. የፌደራል መንግሥትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ማስቆም ካለመቻለም በላይ ወንጀሉን በስም ባለመጥራት በዜጎች ላይ ለሚፈፀመው ጅምላ ፍጅት ተባባሪ በመሆኑ ከተጠያቂነት አያመልጥም፤
4ኛ.በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የማያባራ የዘር ፍጅት መላው ኢትዮጵያውያን እንዲያወግዙ እና ለዘር ፍጅት ሰለባ ቤተሰቦችና ለመላው የአማራ ሕዝብ ፈጣሪ መፅናናትን እንዲሰጣቸው ተመኝቷል፤
5ኛ.በየትኛውም ሁኔታና አካባቢ ለሚገኙ የሀገሪቱ ዜጎች መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት አስፈላጊውን የሕግ ከለላና ጥበቃ እንዲያደርግ ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክልሎች ተዘዋውረው የመሥራት ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው መኢአድ ጥሪውን አቅርቧል።
ዘጋቢ:- ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
