የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ጉባዔ እያካሄደ ነው፡፡

187
የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ጉባዔ እያካሄደ ነው፡፡
ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የምክር ቤቱ ዋና አፈጉባዔ ወርቅሰሙ ማሞ‹‹17ኛ መደበኛ ጉባዔውን የምናካሂደው ሁላችንም ስንተባበር የሚያምርብን፤ በጋራ ስንሰለፍ አንፀባራቂ ድል ማስመዘገብ የምንችል መሆናችንን በተግባር በአሳየንበት ወቅት በመሆኑ ነው›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በትላንት ችግር የማንቆዝም፤ በዛሬ ድል የማንሰክርና የማንፎክር መጭውን ትውልድ አስበን ለመሥራት በተዘጋጀንበትና አትዮጵያዊነት ከፍ ባለበት ወቅት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ዋና አፈጉባዔዋ የሀገራችን ጠላት የሆነው ትህነግ የሉዓላዊነትና የኩራታችን መገለጫ በሆነው የመከላከያ ሠራዊትና በአማራ ክልል ሕዝቦች ላይ በከፈተው ጦርነት በተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜ ለተወሰደው ርምጃና ለተገኘው ድል ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምሰጋና አቅርበዋል፡፡
በሕግ ማስከበር ዘመቻም የወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና የራያ አካባቢ ሕዝቦች ባለፉት ዓመታት በትህነግ አሸባሪ ቡድን፤ የአማራነት ማንነታቸው ተጨፍልቆ የሰው ልጆች ሊሸከሙት የማይችሉት ግፍና በድል ሲደርስባቸው ቆይተዋል፤ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸው በመታፈኑ ይህንን በደል ላለመሸከም ትግል ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆኑም በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ እንዲሁም ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በከፈሉት መስዋዕትነት ነፃነት ተጎናፅፈዋል ብለዋል፡፡ ለዚህም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በሕግ ማስከበር ዘመቻው ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራን፣ ባለሃብቶች፣ አርሶ አደሮችና ሁሉም ሕብረተሰብ ያደረገው ትብብር አንድነታችንን ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
አሁንም የትህነግ ፍርስራሾችና ኦነግ ሸኔ ሀገር ለማፍርስ ባላቸው ፍላጎት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የአማራን ሕዝብ ዘርን መሰረት በማድረግ እያጠቁ ናቸው፤ ይህንን ጥፋት ለማስቆም መንግሥት አጥፊዎችን በሕግ ለመጠየቅ እየተሞከረ ቢሆንም አሁንም በተሟላ መልኩ ሰዎች በሰውነታቸው ተከብረው እንዲኖሩ እየተደረገ አይደለም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉም ተከባብሮ የሚኖርባት ሀገር እንድትሆን በማድረግ በኩል ገና ብዙ የአስተሳስብና የተግባራ ሥራ የሚቀር ስለሆነ ታቅዶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የትግራይና የአማራ ሕዝቦች በኢትዮጵያዊነት የሚኮሩ በደምና በአጥንት የተሳሰሩ፣ በሃይማኖት፣ በባህል በሥነ ልቦና እንዲሁም በሀገረ ግንባታ ሂደት በርካታ ሥራዎችን የሥሩ፤ በአንድ ጉድጓድ የተቀበሩ ሀገር ያቆሙ ሕዝቦች ናቸው ያሉት አፈጉባዔዋ የትህነግ አሸባሪ ቡድን መወገድ ሁለቱም ሕዝቦች በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በዲሞክራሲ ግንባታ ከመቼውም በላይ ተቀራርበው በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ከገጠሙት ችግሮች በመውጣት የክልሉን ሰላምና ልማት ለማጠናከር በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ያደርገው ጥረት የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ያለውን የሰውና ውስን ሀብት በማቀናጀት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች፣ የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከልና ከሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ሕዝብን አስተሳስሮ ለመሥራት የተደረገው ጥረት ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡ የሕዝብን ድጋፍም እንደ ትልቅ አቅም በመውሰድ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
አሁንም በሕዝብ ላይ ያለው የኑሮ ውድነት ጫና ትኩረት ይሻል፤ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ያለው የዋጋ ጭማሪ ሕዝቡን እያማረረ በመሆኑ ለሕዝብ ጥቅም በማሰብ መሥራት አለበት ብለዋል።
ዋና አፈ ጉባዔዋ ምርጫ ለሀገራችን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ምርጫ ሲመጣ ለሕዝብ አስቦ ለመልካም ሥራ መዘጋጅት እንደሚጠበቅና በሕዝቡ ውስጥ ምንም ዓይነት ወከባ ሊፈጠር እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተማዓኒ፣ በሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኝ ማድረግም ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሥልጣኔ መገለጫም ይህ ነው ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሀገር መምራት የሚቻለው ሀገር ሲኖር በመሆኑ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ሀገርን ከጥፋት ለመከላከል በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article85 በመቶ የሚሆነው የእንቦጭ አረም መወገዱን የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
Next articleበአማራ ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን ሊያመጡ በሚችሉ ዘርፎች ላይ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መሥተዳደር አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ፡፡