
ለሁላችን ነጋ፡፡ ሩጫችን ግን ተለያዬ፡፡ ብዙዎች ከቤታቸው አልወጡም፤ አሁንም ሌላ ብዙዎች ቤተ ዘመድ ቤት ጥየቃ ላይ ናቸው፤ ጥቂቶች በልዩ ልዩ ምክንያት ለበዓላት ተነጥለዋል፡፡ ለበዓላት ተችረው በዓላትን በደስታ ማሳለፍ የማይችሉ ጥቂቶች ደግሞ እንደምን አደራችሁ፣ አለያም አረፈዳችሁ የሚል ድምፅን በመሻት በየጉራንጉሩ ይጠብቃሉ፡፡ ህይዎት እንደዚህ ናት ‹‹ጉራማይሌ፡፡››
ግን እኮ የአዲስ ዓመት መባቻ ለሁላችንም የበዙ ቀናትን ለመኖር የተስፋ ስንቅ የምናድስበት የለውጥ ቀን ናት፡፡ ዘመኑን በአዲስ ተስፋ እና በአዲስ ጥረት ስኬታማ ለማድረግ የምናደርገው የለውጥ ሂደት አልፋ ናት፡፡ ለውጡ አዕምሯዊ እና ራሳችንን ለመቀየር ፅኑ ፍላጎት ያለን በመሆኑ የሰጠነው ትርጉም ነው፡፡ ደስታ የበዓሉ አይነተኛ የለውጥ ሀይል ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታ እና የምስጋና ቃል አሰሙ›› በማለት በበዓላት ደስታ አይነተኛ ባህሪው እንደሆነ ይነግራል፡፡
ደስታን ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የደስታ ዋጋውም እንዲሁ ቀላል አይደለም፡፡ የሀብት ጉዳይም አይደለም፡፡ ባለን የመደሰት ልማድ እና ጥበብ እንጂ፡፡ ግን እኮ እንኳን ደስታ ሃዘን እንኳ ብቻን አያምርም፡፡ አበው ‹‹አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም›› የሚሉት የአብርሆትን ብርታት ሲያሳዩንም አይደል?፡፡
በዓላት በራሳቸው ለኢትዮጵያውያን በተለየ የተሰጡ የማኅበራዊ መስተጋብሮች ውጤት ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያውያን በዓላትን ለብቻ ማክበር የበዓል ስሜቱን እና ድባቡን እንደማራቆትም ይቆጠራል፡፡ በጋራ ማዜሙ፣ መመሰጋገኑ፣ መልካም ምኞቱ፣ መስተንግዶው ደግሞ አሮጊ ይሉትን ዘመንን ማባረሪያና ማራገፊያ የአዲስ ዘመን መባቻ ትዝታዎች በውስጣችን የሚያስቀሩ ትሩፋቶች ናቸው፡፡ በየጎረቤት መጠራራት፣ ቤተ ዘመድ መጠየቅ እና አንተ ትብስ አንች ትብሽ መባባሉ ልዩ አውድ አለው፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያት ረጂ ያጡ ዜጎችን መጠየቅ እና ለበዓል ቀናቸው የደስታ ምክንያት መሆን ደግሞ የበዓል ቀናችን ጉልላት ነው፡፡ በዓሉ በዓል ሳይመስለው የሚያልፍ ኢትዮጵያዊ እንዳይኖር ደጋግ ኢትዮጵያውያን በየወቅቱ በሚያደርጉት ድጋፍ እውነተኛ የኩራት ምንጮቻችን ናቸው፡፡
በ2012 አዲስ ዓመት መባቻ ላይ መሰል ተግባራት በተለያዩ አከባቢዎች በግልፅም ሆነ በስውር ተከናውነዋል፤ ‹‹ቀኝህ የሚሰጠውን ግራህ አይይ›› አይደል፡፡ እመኑኝ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ደጋግ ነገሮች ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በጣም ትንሽ የሆነውን እና የሰማሁትን ለምስጋና ያህል ላጋራችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህክምና ተማሪዎች ማኅበር በባሕር ዳር ከተማ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተኝተው የሚታከሙ ከ400 በላይ ከሚሆኑ ወገኖቻቸው ጋር በዓልን አብረው ውለዋል፡፡ የተሰበረን የሰው ልጅ በፍቅር ከማከም በላይ ምንስ ሐኪምነት ይኖራል? በባሕር ዳር ከተማ ዋና ዋና መንገዶች ላይም ጎንበስ ብለው የነዋሪውን ጫማ የማፅዳት ሥራን ሰርተዋል፤ ‹‹ትህትናን ጫማው ያደረገ ምስጉን ትውልድ፡፡›› ተማሪዎቹ ‹‹የመቅደም ሚስጥሩ መጀመር›› መሆኑ ገባቸውና በዓልን በእጥፍ ድርቡ ‹‹ተደስተውና አስደስተው›› አሳለፉት፡፡ ዋጋችሁ በሰማይ ነው ብለናል፡፡
ሌላም አለ! በባሕር ዳር ከተማ ከፋሲሎ ክፍለ ከተማ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ30 አረጋውያን 12 ሺህ ብር በመስጠት አለኝታ ሁነዋል፡፡ ወዳጀ ‹‹በዘመንህ የቸርከው ለአረጋዊነት ቁጠባ ነው››፣ ተፈጥሮ የሰጧትን ትሰጣለች ብለን አይደል ትናንት? ‹‹ደግነት መስማት የተሳናቸው የሚሰሙት እና አይነስውራን የሚያዩት ቋንቋ ነው›› ይሏል ይህ ነው፡፡
በጦሳ ስር ንግስት የአብሮነት ከተማ የፍቅር መዲና የሙሃባ ሰፈር እንደሆነች በሚነገርላት ደሴ አንድ በጎ ነገር ሹክ ልበላችሁና እንስነባበት፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ እና ፍሬው አረጋውያን እና በጎ አድራጎት የተቀናጀ ልማት ማህበር ከ80 በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ አረጋውያን የምሳ ግብዣ እና የሙሉ ልበስ አልባሳት ስጦታም አበርክተውላቸዋል አሉ፡፡
ሁላችሁን ዘመናችሁ ይባረክ በለን ብንሰናበትስ?
‹‹ዘመናችሁ ይባረክ!››
መልካም አዲስ ዓመት፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ