በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ።

234
በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ።
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል።
በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት የወሰደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ የተለያዩ የዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማትና የጁንታው ቡድን ባናፈሰው ፕሮፓጋንዳ አንዳንድ ዓለምአቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት እውነታውን ባለገናዘበ መልኩ እየወሰዱት ያለውን ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወሙ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባካሄዱት ሰልፍ ገልጸዋል፡፡
በሀገር ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳረፍ የከፈቱትን ያልተገባና ከእውነት ያፈነገጠ ጫና እንደሚቃወሙም ሰልፈኞች አስታውቀዋል፡፡
በመላው ካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት በኦታዋ፣ ሞንትሪያል፣ በቶሮንቶ፣ በክችነር፣ በሎንዶን ኦንታሪዮ፣ በኤድመንተን፣ በሊትብሪጅ እና በካልጋሪ ከተሞች ነው ሰልፉ ትላንት የተካሄደው፡፡
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡ ተቋማትና ሀገራት ድርጊታቸውን እንደሚቃወሙና የጁንታው ቡድን በንጹሃን ላይ ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ እንደሚያወግዙ ሰልፈኞቹ በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ ለወሰደው እርምጃ ያላቸውን ድጋፍም ገልጸዋል፡፡
ሰልፈኞች በወቅቱም የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት በተለይም የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባላት የሆኑት የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ መንግሥታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባትና የማይገባ ጫና ከመፍጠር እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲደግፉ የሚያሳስብ ደብዳቤም አቅርበዋል፡፡
ለቻይና፣ ሩስያና ህንድ ኤምባሲዎች ደግሞ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ላሳዩት ታማኝነትና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት ላደረጉት ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብቷ መከበር እንዳለበት፣ የሱዳን መንግሥት በወረራ የኢትዮጵያ መሬት መያዙን እንደሚያወግዙ እና በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ የሚጠይቅና ሌሎችም መፈክሮችን በመያዝ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ መግለጻቸውን ከካናዳ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የ2013 ግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው፡፡
Next article85 በመቶ የሚሆነው የእንቦጭ አረም መወገዱን የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡