
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የ2013 ግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው፡፡
ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2013 ዓ.ም (አብመድ)
የአማራ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዙር ስድስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ጉባዔ እያካሄደ ነው።
አቶ አገኘሁ የሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተጠናቆ በአዲስ የ10 ዓመታት መሪ እቅድ ውስጥ የ2013 በጀት ዓመት እቅድ በማዘጋጀት የክልሉን ሕዝብ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የቆዩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱበት እና የተለየ ርብርብ የሚደረግበት ዓመት መሆኑንም ርእሰ መሥተዳድሩ ጠቅሰዋል፡፡
ባለፈው ግማሽ በጀት ዓመት የሕዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ሲደረግ እንደነበረም አንስተዋል፡፡
የክልሉን የልማት እና የእድገት ጉዞ የሚፈታተኑ፣ የሠላም እና ጸጥታ ችግሮች አጋጥመው እንደነበርም ርእሰ መሥተዳድሩ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡
የትህነግ የጥፋት እና የክህደት ቡድን በፈጸመው ወረራ ምክንያት ወደ ማይፈለግ ጦርነት መገባቱንም አንስተዋል፡፡ በየደረጃው ያለው የጸጥታ መዋቅሩ እና የፖለቲካ አመራሩ እንዲሁም የአማራ ሕዝብ የሥነ ልቦና ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ በመሆኑ የትህነግ የጥፋት እና የክህደት ቡድን የሠነዘረውን የማጥቃት ሙከራ በሚገባ ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የተፈጠረው ወቅታዊ አለመረጋጋት በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በአገልግሎት ዘርፉ እና በአጠቃላይ ልማታዊ አስተሳሰብ ላይ ያስከተለውን ጫናና ተጽእኖ በመቀነስና በመቀልበስ የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል እና እቅዱን ለመፈጸም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
