
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ከደጋፊዎቹ ጋር እየተወያዬ ነው፡፡
አብን በአሶሳ ከተማ ከደጋፊዎቹ ጋር እየተወያዬ ነው፡፡

ውይይቱ በአብን የፖለቲካ ፕሮግራምና ግቦች፣ አማራጭ ፖሊሲዎች፣ እንዲሁም በአማራ ብሔርተኝነት ጉዞና ግቦች ላይ ያኮረ መሆኑን የንቅናቄው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ነግረውናል፡፡
በወቅታዊና ስትራቴጂካዊ፣ አካባቢያዊ፣ ሀገራዊና ቀጠናዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ገለጻ እንደሚደረግና ከደጋፊዎችና ከአባላት ለሚነሱ የግልጽነት ጥያቄዎች ማብራሪያ እንደሚሰጥም ነው አቶ ክርስቲያን ለአብመድ የተናገሩት፡፡
ውይይቱ ከሕዝቡ በንቅናቄው የፖለቲካ አጀንዳዎች ውስጥ እንዲካተቱ የሚነሱ ሐሳቦችን ለማግኘት እንደሚረዳና የአማራ ሕዝብ የኅልውና ጥያቄዎች ላይ የጋራ አረዳድ ለመፍጠር እንደሚያግዝ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የአሶሳውን ውይይት የአብን ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ በለጠ ሞላ፣ የአብን የሥራ አስፈጻሚ የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትና የንቅናቄው የምዕራብ ኢትዮጵያ ዞን በጋራ እየመሩት ነው፡፡
ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት