«የሱዳን ሕዝብ አልሲሲን የተቃወማቸው ግብጽ ፍላጎቷን በሱዳን ለማስፈጸም እያሴረች መሆኑን በመገንዘብ ነው» አቶ ሀሊ ያሂያ ሱዳናዊ የሚዲያ ባለሙያና የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ

202
«የሱዳን ሕዝብ አልሲሲን የተቃወማቸው ግብጽ ፍላጎቷን በሱዳን ለማስፈጸም እያሴረች መሆኑን በመገንዘብ ነው» አቶ ሀሊ ያሂያ ሱዳናዊ የሚዲያ ባለሙያና የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 01/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሱዳን ሕዝብ ፕሬዚዳንት አልሲሲን የተቃወማቸው ግብፅ ፍላጎቷን በሱዳን በኩል ለማስፈጸም እየሠራች ያለውን ሴራ በመንቀፍ እንደሆነ አቶ ሀሊ ያሂያ የሚዲያ ባለሙያና የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ አስታወቁ።
አቶ ሀሊ ያሂያ እንደገለጹት፣ በቅርቡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ካርቱም በተገኙበት ወቅት ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ የገጠማቸው ግብፅ ፍላጎቷን በሱዳን ላይ ጭና ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገውን ሴራ በመቃወም ነው።
ግብፅ በሰሜን ምሥራቅ በኩል የሱዳንን ሰፊ መሬት በጉልበት ወራ መያዟ ሕዝቡን እያስቆጨው ያለ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ሀሊ፣ ግብፅ አሁን የሱዳን ተቆርቋሪ መስላ መቅረቧ ለሱዳን አስባ አለመሆኑን ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል ብለዋል።
የሱዳን ሕዝብ የህዳሴው ግድብ መገንባት ጥቅም እንደሚሰጣቸው ያውቃሉ ያሉት አቶ ሀሊ፣ ግብፅ የአስዋንን ግድብ በገነባችበት ጊዜ 27 ሰፈራ መንደሮች እና 500 መቶ ሺህ ሱዳናዊያን ተፈናቅለዋል፤ ለዚህ ሁሉ ጥፋታቸው ምንም ዓይነት ካሳ ሳይሰጡ ይባስ ብለው መሬታቸውን በመውረራቸው የሱዳን ሕዝብ እስከ ዛሬ ድረስ እንደሚቃወማቸው አመልክተዋል።
ግብፅ ከሱዳን መከላከያ ሠራዊት ጋር ስምነት መፈጸሟንና የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውን የሱዳን ሕዝብ እያወገዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግብፅ ሱዳንን ወደ ጦርነት የምትገፋት የህዳሴው ግድብን መጠናቀቅ ተከትሎ ኢትዮጵያ በቀጣናው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን ትይዛለች ከሚል ስጋት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ተቃውሞው በሱዳን እና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌለ ያሳየና የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ምን ማድረግ እንዳለባቸው አቅጣጫን ያመላከተ ክስተት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሀሊ ፣ ሱዳን እና ግብፅ ሕብረት በመፍጠር የህዳሴውን ግድብ ለማስተጓጎል ሲንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ተለያይተው በር ሊከፍቱ አይገባም ብለዋል።
ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ ፈላጭ ቆራጭ እኔ ነኝ የሚል አቋም ይዛ ሱዳን 18 በመቶ ብቻ እንድትጠቀም ስታደርግ ነበር ያሉት አቶ ሀሊ፣ ዛሬ ኢትዮጵያን ለመገዳዳር የተነሳችው በሱዳን ላይ ያሳየችውን የበላይነት ለመድገም በማሰብ ነው። ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታስበውን ያህል ግብፅ እንደማታስብ አስታውቀዋል።
ሱዳናውያን ሰላምና ውኃ ከኢትዮጵያ እንደሚመነጩ ያውቃሉ ያሉት አቶ ሀሊ፣ የሱዳን ምሁራንና ሕዝብ ለኢትዮጵያ መልካም አስተሳሳብ አላቸው። ከመቶ ዓመታት በላይ ሳይፈታ የቆየ የድንበር ጉዳይ ዛሬ ምክንያት የተደረገው ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የውኃ ሙሌት አንዳታከናውን ለማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል።
ዛሬ የሱዳን ወዳጅ መስላ የቀረበችው ግብፅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ማከናወን የሚገባትን የሱዳንን ጉዳይ በደኅንነት ቢሮዋ ጥብቅ ክትልል ስር እንደምታደርግ ጠቁመው፣ግብፅ ሱዳንን ለጥቅሟ ስትል ተገቢ ያልሆነ ወዳጅነት ብትመሰርትም ሕዝቡ አይደግፋትም ብለዋል።
ሱዳን የግብፅን ፍላጎት ለማሟላት ስትል ከኢትዮጵያ ጋር የኖረ ጉርብትናዋን ማጣት የለባትም። ሁለቱ ሀገራት የኖረ ሰላማዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል ለመጪው ትውልድ ወንድማማችነታቸውን ማስተላለፍ እንዳለባቸው ማስታወቃቸውን ኢትዮ ፕረስ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝብ መብቶች ኮሚሽን ከኢሰመኮ ጋር በመተባበር በትግራይ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እንዲያጣራ ፈቃደኛ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next article“እየተከለሰ ያለው የኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂና የመሪነት ሚና እንዲኖረው የሚያስችል ነው ” የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ(ዶ.ር)