የዋጋ ንረት ኑሯቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

225
የዋጋ ንረት ኑሯቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) በነፃ ገበያ ሥርዓት የገበያው ፍላጎትና አቅርቦት መመጣጠን ባለመቻሉ ዜጎች በኑሮ ውድነት እየተፈተኑ ነው፡፡ በቀናትና በወራት ልዩነት በምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገባቸው መሆኑን አብመድ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ሀርጓ ስጦታው በባሕር ዳር ከተማ የዕለት የፍጆታ ምርቶችን ሲገዙ አግኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ እሳቸውም የዋጋ ጭማሪ የኑሮ ሁኔታውን ከባድ እያደረገው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “ዛሬ የገዛሁበትን ዋጋ ነገ አላገኘውም፤ ይህም ይቀጥላል፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የምንገኝ ሰዎች መኖር አልቻልንም፤ ከታክሲ ጀምሮ ያልጨመረ ዋጋ የለም፤ አምስት ብር የሌለው ሰው በታክሲ መሄድ አይችልም፤ መኮሮኒ ከ23 ብር 40 ብር ገብቷል፤ አምስት ሊትር ዘይት ከ400 ብር ወደ 500 ብር ገብቷል፤ ነጋዴዎችን ስለጭማሪው ስንጠይቃቸውም ጨመረብን ነው የሚሉት” ሲሉ የዋጋ ንረቱን በምሬት አስረድተዋል፡፡
ይህም መንግሥት ገበያውን መቆጣጠር ባለመቻሉ ነው ባይ ናቸው፡፡
በባሕር ዳር ከተማ በእህል ንግድ የተሠማሩት አቶ አራጋው አላምር ለዋጋ ንረት እንደምክንያት ያነሱት በቂ የምርት አቅርቦት አለመኖርን፣ አርሶ አደሮች ለሸማች ማኅበራት ከመሸጥ ይልቅ ወደ ከተሞች ገብተው በህገ ወጥ መንገድ መሸጥና የህገ ወጥ ነጋዴዎች መበራከት ነው፡፡
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ችግሩን ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የቢሮው ምክትል ኀላፊ ተዋቸው ወርቁ ለዋጋ ንረቱ የንግዱ ማኅበረሰብ አመለካከት አለማደጉ፣ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የእንስሳት ውጤቶች በበቂ መጠን ገበያ ላይ አለመቅረብን ጠቅሰዋል፡፡
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት አለመቻላቸው፣ የኪራይ፣ የትራንስፖርትና የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ ሕገ ወጥ ንግድ መበራከት፣ ምርቶችን መከዘን፣ መደበቅ፣ ተመሳጥሮ ዋጋ መጨመር፣ ያለ ፈቃድ መነገድ፣ የደላላ ጣልቃ ገብነት፣ የአቻ ግብይት መኖር እና መሰል ችግሮች ለዋጋ ንረቱ ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
እንደ ምክትል ቢሮ ኀላፊው ማብራሪያ ችግሩን ለመከላከል በሚያደረጉት ጥረት የሕግ ማቀፍ ክፍተቶች አሉ፡፡ በተለይም የትርፍ ህዳግ ገደብ በሕግ አለመቀመጡ ለቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የንግድና ገበያ ልማት ሴክተሩ የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና ሎጂስቲክስ ችግር እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡
ምክትል ኀላፊው እንደ መፍትሔ ብለው ከነገሩን መካከል በክልሉ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የነዳጅ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ በክልልና በዞን ከተሞች በተመረጡ ምርቶች ላይ የተቀመጠውን ከፍተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ለአብነተም በባሕር ዳር ከተማ 4 ሺህ 400 ብር ይሸጥ የነበረውን የነጭ ጤፍ ዋጋ 3 ሺህ 917 ብር እንደሚሸጥ አስታውቀዋል፡፡
አቶ ተዋቸው እንዳሉት “በመንግሥት የተመን ዋጋ የሚሸጡ ሸቀጦችን ያለምንም ብክነት ለኅብረተሰቡ ማሰራጨት፤ የክልሉ ምክር ቤት ያጸደቀውን የዋጋ ንረት መቆጣጠሪያ መመሪያ ቁጥር 04/2013 ተግባራዊ ይሆናል፤ ተጨማሪ ተዘዋዋሪ ፈንድ በማመቻቸት የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በቂ ምርት እንዲገዙ ይደረጋል፤ የሱቅና የመጋዝን ቦታ ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ይመቻችላቸዋል፤ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓትን በመዘርጋት የዋጋ ንረትን ለመከላከል ይሠራል” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“አንድነት ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ በዋሽንግተን ዲሲና በኒውዮርክ ግዛቶች ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ ነው፡፡
Next article“የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝብ መብቶች ኮሚሽን ከኢሰመኮ ጋር በመተባበር በትግራይ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እንዲያጣራ ፈቃደኛ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ