በምርጫ ወቅት ዳኞች በመርሕ ላይ ተመስርተው ተገቢውን የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አብዬ ካሳሁን አሳሰቡ፡፡

152
በምርጫ ወቅት ዳኞች በመርሕ ላይ ተመስርተው ተገቢውን የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አብዬ ካሳሁን አሳሰቡ፡፡
ባሕር ዳር: የካቲት 30/2013 ዓ.ም (አብመድ)
የምርጫ ክርክር ሂደቶች በሚመሩበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለዳኞች በባሕር ዳር ከተማ እየተሰጠ ነው፡፡ የስልጠናው ዓላማ በምርጫ የሕግ ማዕቀፎች እና የምርጫ ክርክሮች በሚመሩበት ሁኔታ ላይ ዳኞች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡
ስልጠናውን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አብዬ ካሳሁን አስጀምረዋል፡፡ ነጻና ገለልተኛ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የዳኞች የዕለት ከዕለት ተግባር ቢሆን በምርጫ ጉዳዮች ክርክር ጊዜ የተለየ ገጽታ እንደሚኖረው አቶ አብዬ ለተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ የምርጫ ጉዳይ ክርክሮች እንደማንኛውም የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ክርክሮች ናቸው፤ ነገር ግን የምርጫ ጉዳይ ክርክሮች ፉክክር ጠበቅ ያለ ነው፤ የሁለት ተከራካሪዎች ብቻ ሳይሆን በደጋፊ ኅብረተሰብ መካከል ጭምር የሚደረግ ክርክር መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
አቶ አብዬ እንዳሉት የምርጫ ጉዳይ ክርክርን በትኩረት የሚከታተል አካል ብዙ ስለሆነ ጫናው ይከብዳል፤ በዚህም ከሌሎች የክርክር ሂደቶች የተለየ ያደርገዋል፡፡ የምርጫ ክርክር በጊዜ የተገደበ በመሆኑ ፈጥኖ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህም የምርጫ ጉዳይ ክርክሮች የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን አመላክተዋል፡፡
የምርጫ ጉዳይ ክርክሮችን ለመምራት የወጡ ሕጎችን በአግባቡ መገንዘብ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን በማንሳትም ስልጠናው ለዚህ ዓላማ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ፍርድቤቱ ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት የዳኞች ነጻነትና ገለልተኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥብቅ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ወቅቱ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ መመርመርና ትክክለኛ ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስፈልግበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ለዚህም በምርጫ ወቅት ዳኞች በመርሕ ላይ ተመስርተው ተገቢውን የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡
ሰልጣኞች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አብመድ ያነጋገራቸው ሰልጣኞችም የምርጫ ክርክርን በውጤታማነት መምራት የሚያስችል ግንዛቤ ከስልጠናው እንሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ በምርጫ ወቅት የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከባሕር ዳር እና አካባቢዋ፣ ከምስራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች፣ ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንዲሁም ከመተከል ዞን የተውጣጡ ዳኞች ተሳትፈዋል፡፡
በተጨማሪም በደብረ ብርሃን፣ በደሴና በጎንደር እየተሰጠ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየተሰጣቸው እውቅና እና ሽልማት ለበለጠ ኀላፊነት እንደሚያነሳሳቸው ኢትዮ-ቴሌኮም ያመሰገናቸው ሴት መምህራን ገለጹ፡፡
Next article“አንድነት ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ በዋሽንግተን ዲሲና በኒውዮርክ ግዛቶች ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ ነው፡፡