
የተሰጣቸው እውቅና እና ሽልማት ለበለጠ ኀላፊነት እንደሚያነሳሳቸው ኢትዮ-ቴሌኮም ያመሰገናቸው ሴት መምህራን ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ ኢትዮ-ቴሌኮም በ2012 ዓ.ም የሥራ አፈፃፀማቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ሴት መምህራንን አመስግኗል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ 50 ላፕቶፕ ኮምፒውተር እና 200 ስማርት ፎን የሞባይል ቀፎ ለ250 ሴት መምህራን አበርክቷል፡፡
በኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የ2013 ዓ.ም ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ ለ22 ሴት መምህራን እውቅና ሰጥቷል፡፡ አምስቱ ሴት መምህራን የላፕቶፕ ኮምፒውተር ተሸላሚ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 17 ሴት መምህራን ደግሞ የሞባይል ስማርት ፎን ተበርክቶላቸዋል፡፡
መምህርት እመቤት ጌታነህ ከእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ፊታውራሪ ዘንጋው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና መምህርት ባንችአምላክ ጋሻው ከሊቦ ከምከም ወረዳ ይፋግ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የመጡት፡፡
ሁለቱ መምህራን በ2012 ዓ.ም በክልሉ የተሻለ አፈፃፀም ካስመዘገቡ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የተሰጠን እውቅና እና ሽልማት እኛን ብቻ ሳይሆን ከእኛ ጀርባ ያሉ በርካታ ሴት መምህራንን የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡ እውቅናው ለነገ ሥራ አደራ ስለሆነም ለበለጠ ኀላፊነት የሚያነሳሳ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጂናል ዳይሬክተር አቶ አበበ ጥሩነህ ኢትዮ-ቴሌኮም በበርካታ ማኅበራዊ ኀላፊነቶች ላይ ተሳታፊ መሆኑን ጠቅሰው በዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ላይ ሴት መምህራንን አመስግነናል ነው ያሉት፡፡ አምስት ላፕቶፕ ኮምፒውተር እና 17 ስማርት ፎን በሰሜን ምዕራብ ሪጂን አካባቢ ላሉ ሴት መምህራን ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮ- ቴሌኮም በቀጣይም ማኅበራዊ ኀላፊነቱን አጠናክሮ ይወጣል ያሉት አቶ አበበ የሁሉም ነገር መሰረት ለሆኑት መምህራን ከዚህ በላይ ደግሞ ሴቶችን ማመስገን በመቻላችን ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
