የደብረታቦር የባሕል ማዕከልና አዳራሽ ቢሮ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ከተያዘለት በጀት ከ30 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።

158
የደብረታቦር የባሕል ማዕከልና አዳራሽ ቢሮ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ከተያዘለት በጀት ከ30 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።
ባሕር ዳር፡ የካቲት 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) የደብረታቦር የባሕል ማዕከልና አዳራሽ ቢሮ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ከ30 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል። የጽሕፈት ቤቱ ቴክኒካል ማናጀር ኢንጅነር ብርሃኑ ታደሰ እንደነገሩን ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ ወደ ተግባር ቢገባ 80 በመቶ ግንባታውን ማከናወን ይቻል ነበር። ይሁን እንጅ የግንባታ ቦታው ከሶስተኛ ወገን ባለመጽዳቱ በተፈጠረው የግንባታ መዘግየት ባሁኑ ወቅት 40 በመቶ ነው ማከናወን የተቻለው።
በጊዜው ክፍያ አለመፈጸም ለመጓተቱ በሁለተኛ ምክንያትነት ተቀምጧል። በዚህ ወቅትም ለመሥራት ከታቀዱት ሦስት ፎቆች የባለ ሁለት ፎቅ ግንባታ የሚሰራበት ቦታ ከሶስተኛ ወገን ባለመጽዳቱ ግንባታውን መጀመር አልተቻለም። ባለ አራተኛ እና ባለ ስድስተኛ ፎቅ ሥራ ግን እየተከናወነ ይገኛል። ባለ ስድስተኛ ፎቅ ግንባታ ስትራክቸሩ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል፤ የፎቁ የመጨረሻ የጣራ ሥራ ሙሊት እየተከናወነ ይገኛል። ባለ አራተኛ ፎቅ ግንባታ ደግሞ የጣራ ሥራ ብቻ ነው የሚቀረው። በዚህም ከአጠቃላይ ከፕሮጀክቱ ሥራ 40 በመቶ ብቻ ማጠናቀቅ ተችሏል።
ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ የግንባታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ሥራ አስኪያጁ አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ ግንባታው ሲጀምር 280 ብር የነበረው ሲሚንቶ በዚህ ወቅት እስከ 700 ብር መድረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል። በተለይ ደግሞ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያሳየ ነው። ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ሶስት ዓመታት የሚጠጋ ጊዜ ያስፈልጋል ተብሏል። ይህም ከ30 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ሥራ አስኪያጁ ነግረውናል። ይህም ተጨማሪ በጀት ስለሚጠይቅ በሀገር ሀብት ላይ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ ነው ያስገነዘቡት።
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንዴ መሠረት እንደገለጹት ተቋራጩ ቦታውን ከሶስተኛ ወገን ሳይጸዳ መረከቡ ለስራው መጓተት ምክንያት ሆኗል። ቀሪው ሶስተኛ ፎቅ የሚገነባበትን ቦታ ከሶስተኛ ወገን ለማጽዳት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። በግንባታው መጓተት ምክንያት የመጣው የዋጋ ልዩነትም ለክልሉ መንግሥት መቅረቡን እና ችግሩ እንደሚፈታ ነግረውናል።
የባሕል ማዕከል ግንባታው በ3 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ነው። ለግንባታው 193 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን በሦስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታስቦ ነበር ወደ ሥራ የተገባው። ማዕከሉ የተለያዩ የባሕል ዕቃዎች የሚጎበኙባቸው የክምችት ክፍሎች፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው አዳራሾች እና ቢሮዎች የሚኖሩት ባለ ሁለት፣ ባለአራት እና ባለስድስት ፎቅ ሦስት ሕንጻዎች ይኖሩታል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ መግባቱ የሱዳን ሕዝብ ፍላጎት ሳይሆን የሌላ አካል አጀንዳ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
Next articleየተሰጣቸው እውቅና እና ሽልማት ለበለጠ ኀላፊነት እንደሚያነሳሳቸው ኢትዮ-ቴሌኮም ያመሰገናቸው ሴት መምህራን ገለጹ፡፡