
ለምርጫው ሰላማዊነት ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባ የጋሞ አባቶች ተናገሩ።
ባሕር ዳር: የካቲት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ምርጫውን አስመልክቶ ኢዜአ ካነጋገራቸው የጋሞ አባቶች መካከል አቶ ሰዲቃ ስሜ እንዳሉት ሰላም የሁሉም መሠረት በመሆኑ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ህብረተሰቡ የበኩሉን መወጣት አለበት።
ሀገሪቱ በአንድም በሌላ እየተፈታተኑ ያሉ ሁኔታዎችን በመገንዘብ የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል በማለት ሁሉም ለሰላም ከምንም በላይ ማሰብ እንዳለበት ጠቁመዋል።
የጋሞ ህዝብ ሰላም ማስፈን የሚያስችል ባህላዊ እሴት ባለቤት ነው፤ ለዚህም እኔም ከሌሎች የጋሞ አባቶች ጋር በመሆን ለምርጫው ሰላማዊነት እሰራለሁ ብለዋል።
ከዚህ በፊት በነበሩ ምርጫዎች ጫናዎች በመፍጠር በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብቶቻችን ያጣን በመሆኑ ይህ አሁን እንዳይደገም እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አማራጮቻቸውን ብቻ በማቅረብ መወዳደር እንጂ ኀላፊነት የጎደለው ተግባር በመፈጸም የህዝቡን ሰላም ከሚያደፈርሱ ንግግሮችና ቅስቀሳዎች መቆጠብ እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሁሉም ሰው በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የጋሞ አባት ካዎ ሙልጌታ መንሳ ናቸው፡፡
ሰላም ከሌለ የህዝብ ህልውና አደጋ ላይ ስለሚወድቅ እያንዳንዱ ዜጋ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከጋሞ አባቶች ጋር በመተባባር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸው በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ አባቶች የመሪነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ካዎ ጾና አባይነህ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፀረ-ሰላም ሃይሎች በፈጠሩት ሁከት የህዝቡ ደኀንነት አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር አስታውሰዋል።
የህዝቡ ሰላም ሊመለስ የቻለው መንግስት የህግ የበላይነት ለማስከበር ባደረገው ጥረት ቢሆንም ህዝቡ ለአከባቢው ሰላም ያበረከተው ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
