
ሴቶች የኮሮናቫይረስ ለመከላከል በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) እንደ ኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው ውስጥ 39 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው፤ በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ 37 በመቶ ያህሉም ህይወታቸው አልፏል፡፡ ካሁን ቀደም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት ከመዘጋቱ ጋር ተያይዞ የሴቶችና የህጻናት ጥቃት፣ ያለእድሜ ጋብቻ እንዲሁም እርግዝና ጨምሮ እንደነበር ኢንስቲትዩቱ ጠቅሷል፡፡
በዓለም ላይ አንድ ሴት በቤት ውስጥ ክፍያ ሳይኖረው በሚከናወሩ ሥራዎች ከምታሳልፈው ሰዓታት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በተጨማሪ አራት ሰዓታት በተጨማሪ በቤት ውስጥ ሥራ እና እንክብካቤ ያሳልፉሉ፡፡ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 243 ሚሊየን ሴቶች የጾታ ጥቃት እንደደረሰባቸውም አሳይቷል፡፡
የጤናው ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች ከሌላው የማኅበረሰብ አባላት እና የተለያዩ ሥራዎች ላይ ከተሳተፉ ሰዎች ይልቅ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በጤና ሴክተር ላይ ከተሰማሩ ሠራተኞች ውስጥ 70 በመቶ ሴቶች መሆናቸው በዘርፉ ያለውን የሴቶች ተጋላጭነት ከፍተኛ እንዲሆን ማድጉና ሌሎች ምክንያቶች ኮሮናቫይረስ ሴቶች ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ማሳያዎች እንደሆኑ ኢንስቲትዩቱ ጥናቶችን ጠቅሶ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አመላክቷል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚከናወኑ ሥራዎች ለማኅበረሰቡ አርዓያ በመሆንና በማስተማር የማኅበረሰብ ጤና ለመጠበቅ ሴቶች ትልቅ ሚና አላቸው ብሏል ኢንስቲትዩቱ፡፡
ሴቶች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ መንገዶችን በመተግበር ለበሽታው ቁጥጥር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
