
“ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል የያዙት አቋም ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው” ምሁራን
ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) ግብፅና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የያዙት አቋም የዓለም አቀፍ የድንበር ተሸጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ስምምነትን የጣሰ መሆኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ውኃ ሃብት ምርምር ምሁራን አስታወቁ።
በዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ጋድሰንድ ኮኖሮ እንዳሉት የተባበሩት መንግሥታት በድንበር ተሸጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ስምምነት ዙሪያ ያወጣው ሕግ የተፋሰስ ሀገራት ፍትሐዊ አጠቃቀም መርህን እንዲከተሉ ያስገድዳል። በተለይ የአንዱ መጠቀም በሌላኛው የተፋሰስ ሀገር ላይ የጎላ ተፅዕኖ በማያሳርፍ መልኩ መሆን እንዳለበትም ሕጉ እንደሚያመለክት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ሉዓላዊት ሀገር በግዛቷ የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎችን አልምታ የመጠቀም መብት እንዳላት አስረድተዋል። ከተፋሰስ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያሳጣ ስምምነትና ቃል ኪዳን አለመግባቷን ጠቅሰዋል።
ግብፅ ከኢትዮጵያ በሚፈስ ውኃ የመጠቀም መብት እንዳላት ሁሉ ኢትዮጵያም በገዛ የተፈጥሮ ሃብቷ የማትጠቀምበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።
ግብፅ እስካሁን የሄደችበት ርቀት በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ከመተባበር ይልቅ ለማደናቀፍ የውሸት ትርክት ከመንዛት አንስቶ ብድር እስከ ማስከልከል ጥረት ከማድረጓ ባሻገር ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑ ቡድኖችን በገንዘብ ለመደገፍ መንቀሳቀሷ አስነዋሪ ተግባር እንደሆኑ ምሁሩ አብራርተዋል።
የዓባይን ወንዝ እኔ በብቸኝነት ልጠቀም በሚል መውተርተሯና የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራትም እኔ ሰፍሬ በምሰጣቸው ልክ መጠቀም አለባቸው የሚል የተዛባ አቋም መያዟ የዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ መሆኑን አሰታውቀዋል።
በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ከውኃ ድርድር ጋር በተያያዘ እያሳየ ያለው ቀናነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ከዓለም አቀፍ የውኃ አጠቃቀም ሕጎችና መርሆዎች አንፃር ተቀባይነት ያለውና ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ምሁሩ ገለፃ የህዳሴ ግድብ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር፣ ለቀጣናው ሰላምና ብልፅግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። የተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር የወንዙ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ የመልማት መብቷን የሚያስከብር እንዲሆንና የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ጥቅምም የሚያስጠብቅ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሕግ ምሁር ዘሪሁን ቦዳ በበኩላቸው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ”ግብፅና ሱዳን የያዙት አቋም በዲፕሎማሲውም ሆነ ከሕግ ተገቢነት አንፃር ፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
ሱዳን እስካሁን ግልጽ አቋም ባለመያዟ ምክንያት በግብጽ መንግሥት ጫናና ተፅዕኖ ስር በመውደቅ የግብፅን አቋም የማራመድና የመደገፍ አዝማሚያ ማሳየቷ ትዝብት ውስጥ የሚከታት ነው ብለዋል።
በአንፃሩ ከ80 በመቶ በላይ የዓባይ ወንዝ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ለብቻዬ ልጠቀም ሳትል ይልቁንስ በታችኞች ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት በማያስከትል መልኩ በጋራ ለመጠቀም መወሰኗ ተገቢነትና ተቀባይነት እንዳለው አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ሕዝቧን ከተመፅዋችና ከጨለማ ለማውጣት ግድቡን ጥቅም ላይ ማዋል የህልውና እና መብት ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ግዴታም ነው ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ዋና ዓላማ ውኃው ኃይል ካመነጨ በኋላ የራሱን ፍሰት ይዞ የሚሄድ በመሆኑ የሚያደርሰው ጉዳት እንደሌለ የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውኃ ሃብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ሳሙኤል ዳጋሎ ናቸው።
”በ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ እናቶች የማገዶ እንጨት በመሸከም ወገባቸው መጉበጡ ያሳዝናል” ያሉት ዶክተር ሳሙኤል አሁን ላይ የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት በቂ ባለመሆኑ በርካታ ሕዝብ ጨለማ ውስጥ እንደሚኖር አስረድተዋል። እስከ አራት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የግድቡን የውኃ ሙሌት ማጠናቀቅ እየተቻለ መንግሥት እስከ 7 ዓመታት ደረጃ በደረጃ ስለመሙላት ማቀዱ ምን ያህል ፍትሐዊ አካሄድን እየተከተለ መሆኑ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
ባለፉት ጊዜያት ከዓባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ ሱዳን ለዘመናት በጎርፍና ደለል ስትናጥ መቆየቷን ጠቅሰው በቅርቡም በተፈጠረው የጎርፍ አደጋ የበርካታ ዜጎቿን ህይወት መንጠቁን አውስተዋል። ሆኖም የግድቡ መገንባት ሱዳንንና ግብፅን ከጎርፍ እና ግድባቸውንም ከደለል አደጋ ለመታደግ ጉልህ ሚና እንዳለው አምነው ሊቀበሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሰፊ የውኃ ሃብት ስላላት ዓባይን ትተውልን ማለታቸው ጊዜ ያለፈበት ተረት በመሆኑ ግብፅና ሱዳን ከግለኝነት አስተሳሰብ ተላቀው ለዓባይ ዘላቂ ልማት ድጋፋቸውንና ትብብራቸውን ማሳየት እንዳላባቸው ገልዋል።
የኢትዮጵያ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ሳይንሳዊ እውነታን ይዘው ድምፃቸውን በማሰማት የበኩላቸውን እንዲወጡና ሕዝቡም የጀመረውን ድጋፍ ከዳር እንዲያደርስም ምሁሩ አስተያየታቸውን መስጠታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
