
ሴቶች የአመራርነትና የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሴቶችን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ አስናቁ ደረስ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን (ማርች 8) አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ110ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ45ኛ ጊዜ፣ በአማራ ክልል ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ “የሴቶችን መብት የሚያከብር ትውልድ እንፍጠር” በሚል መሪ መልዕክት በክልል ደረጃ በባሕር ዳር ከተማ የካቲት 30/2013 ዓ.ም ይከበራል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ አስናቁ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በየዓመቱ በመድረክ ብቻ ይከበር እንደነበርና ይህም ውጤት አለማምጣቱን አውስተዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ሴቶች በቡድን እና በተናጠል በመቆጠብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሴቶችን የሥራ ጫና የሚቀንሱ ልዩ ልዩ ቴክኖሎጅዎችን በማስተዋወቅ በኩልም ሰፊ ሥራ መሠራቱን ኀላፊዋ ገልጸዋል፡፡
ሴቶች ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ኀላፊዋ ጠቅሰዋል፡፡
ወይዘሮ አስናቁ ሴቶች የአመራርነትና የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ የሴቶችን ግንዛቤ ማሳደግም ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ሴቶች ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር በራሳቸው እንዲታገሉ ማስቻልም ከሁሉም የሚጠበቅ ነው ብለዋል ኀላፊዋ በመግለጫቸው፡፡
በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ሴቶች በሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚዳስስ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡
ሴቶች በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በመራጭነት፣ በተመራጭንነት እና በምርጫ አስፈጻሚነት በንቃት በመሳተፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በበዓሉ ላይ በተለያዬ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ኀላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡ ሴቶች እንዲሁም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የስምንተኛ ክፍል እና ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እውቅና ይሰጣል ብለዋል፡፡ ተሞክሯቸውን ለሌሎች ያካፍላሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ቀደምትና የአሁን ዘመን ሞዴል ሴቶች ታሪካቸው የሚሰነድበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች፣ ምሁራን፣ ሴቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት ኀላፊዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች በበዓሉ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
