
ኢትዮጵያ በመቀንጨርና በመቀጨጭ ችግር ምክንያት በዓመት 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ታጣለች፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሥርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ትግበራ ላይ የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የምክክር አውደ ጥናት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የተመጣጠነ የምግብ ንጥረ ነገር ያላቸውን ምግቦች አለመመገብ የሚያስከትለውን የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግሮችን ለመፍታት የድህረ-ምርት ብክነት ችግሮች የሚያደርሱት ሀገራዊ ጉዳት አሳሳቢ መሆኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የምግብና የሥርዓተ-ምግብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ሥርጋዊ እንደገለፁት በሥርዓተ-ምግብ መጓደል ችግር ምክንያት የተመጣጠኑ የምግብ ንጥረ ነገሮችን ባለማግኘት የተነሳ በሚፈጠረው የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ በዓመት 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ታጣለች፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በግብርና ዘርፍም በ17 በመቶ የአምራች ኀይል ምርታማነት እንደሚቀንስና ይህም ግብርናውን አቅም በማሳጣት ምርትና ምርታማነት እንዳይጨምር እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡ የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግርን ለመፍታት አርሶና አርብቶ አደሮች ቢያንስ በጓሯቸው አራት ወይም ከአራት በላይ የምግብ ምድቦችን የሚያሟሉ የሰብልና የእንስሳት ምርቶችን በማምረት የተሰባጠረ አመጋገብን እንዲተገብሩ በማስቻል ጤናማና ብሩህ አዕምሮ ያለው አምራች ኃይል መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወንዳለ ሀብታሙ የሥርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ፖሊሲ ከሚያተኩርባቸው ዋና ዋና ጉዳዩች መካከል የምግብ ምንጮችን በዝርዝር መተንተንና በቀላሉ የሚገኙ የምግብ አማራጮችን በተገቢ ሁኔታ እንዲያዙ መስራት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
“ክልሎች ሥርዓተ-ምግብን እንደ ተጨማሪ ሥራ ማየት የለባቸውም” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው የዘርፎች፣ የሴክተሮች እና የክልሎች ዕቅድ ከሥርዓተ- ምግብ ጋር የሚናበብ ስለሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ደረጃውን የጠበቀ ጥራት ያለው ጤናማ ምርት በማምረት ሂደት የራሳቸውን ድርሻ በቁርጠኝነት እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ ገብረመድህን የሥርዓተ-ምግብ ጉዳይ ትውልድን የማዳንና ሀገርን የማስቀጠል ጉዳይ በመሆኑ ጊዜ ሳይሰጠው መሠራት ያለበት ነው ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም ግብርና ሚኒስቴር ትልቁን ድርሻ ለመወጣት እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ ግብርናን ለማዘመን የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ እየተሻሻለ እንደሚገኝ ጠቅሰው የሥርዓተ ምግብ ተኮር ግብርና ትግበራን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የአስር ዓመት እቅድ ተቀርፆ በሁሉም ዘርፎች በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ግብርናን በማዘመን የድህረ-ምርት ብክነትን ለመቀነስ ሁሉንም ዘርፎች ያማከለ የሜካናይዜሽን ሥራ እየተሠራ ይገኛል፤ አርሶ/አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 659 የሜካናይዜሽን መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ሥርዓተ-ምግብን ታሳቢ ያደረገ አዲስ አደረጃጀት መስራቱንና ክልሎችም መነሻ ሀሳብ ወስደው የራሳቸውን አደረጃጀት ለመፍጠር ከወዲሁ አስበው መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የምርምር አካላት የሥርዓተ-ምግብን ችግር የሚፈቱ ምርምሮችን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በማፍራትና የማኅበረሰቡን አኗኗር የሚያሻሻሉ ሥራዎችን በማከናወን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ አቶ ተሰማ መጠየቃቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
