አምስት የአበባ አምራች ኩባንያዎች ተቀናጅተው በሳምንት ሁለት ቀናት 30 ቶን አበባ ማቅረብ ባለመቻላቸው የቀጥታ በረራው አልቀጠለም፡፡

340

አምስት የአበባ አምራች ኩባንያዎች ተቀናጅተው በሳምንት ሁለት ቀናት 30 ቶን አበባ ማቅረብ ባለመቻላቸው የቀጥታ በረራው አልቀጠለም፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 27/2011 ዓ.ም (አብመድ) በአበባ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን አቅም በማሳደግ በቀጥታ ወደ ውጭ እንዲልኩ ለማድረግ እሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የጣና ፍሎራ የአበባ ልማት በአማራ ክልል ባሕር ዳር አካባቢ ወደ ዘጌ በሚወስደው መስመር ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ሥራ ከጀመረ 11 ዓመት ሆኖታል፤ የመጀመሪያ ምርቱን ወደ ውጭ ሀገር መላክ ከጀመረ ደግሞ ስምንት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የአባባ ልማት እስካሁን 37 ሄክታር በማልማት ምርቱን ወደ ውጭ እየላከ ነው፡፡ ቀሪውን በ2020 (እ.አ.አ) በማልማት ሥራ እንደሚያስጀምርም የጣና ፍሎራ የእርሻ ልማት አስተዳድር ሥራ አስኪያጅ አቶ ክንዳለም ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡
የጣና ፍሎራ የአበባ ልማት 20 የአበባ አይነቶችን ያመርታል፡፡

የአበባ ቀለሞቹም እንደገበያው ፍላጎት እና ወቅት በመመስረት የሚመረቱ ናቸው፡፡ የአበባ ልማቱ በአመት 58 ሚሊዮን ዘንግ በማምረት ከ40 ሚሊዮን እስከ 48 ሚሊዮን ዘንግ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገባ መሆኑንም አቶ ክንዳለም አስረድተዋል፡፡ የጣና ፍሎራ እርሻ ልማት ለ950 ዜጎች የሥራ እንደፈጠረም ነው የገለጹት፡፡ በጣና ፍሎራ የእርሻ ልማት እድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች ውስጥ ወጣት በለጠ ሙሌ እንደተናገረው በተፈጠረለት የሥራ እድል እራሱን እና ወገኑን እየረዳ ነው፡፡ ‹‹እራሴንም ይሁን የስራ እድል የፈጠረልኝን ድርጅት ለመለወጥ በቁርጠኝነት እሰራለሁ›› ያለው ወጣት በለጠ ከአበባ እርሻ ልማቱ ጎን ለጎን የሚሰራው የአትክልት ልማት እና ፍራፍሬ ጥሩ ዕቀውቀት እንዳስጨበጠው ነግሮናል፡፡

የአበባ ልማቱ በውጭ ምንዛሬም ይሁን በሥራ ዕድል ፈጠራ ፋይዳው ጉልህ ሆኖ እያለ የመንገድ ብልሽት እና የመብራት መቆራረጥ ሥራው ላይ ተጽኖ እየፈጠረ እንደሆነ ነው አቶ ክንዳለም ለአብመድ ያስታወቁት፡፡ “የአበባ ልማት ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው፤ አበቦችን የምንመግበው በመብራት ነው፤ ቆርጠን ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ የምናስቀምጣቸው በመብራት ነው፤ አበባ ተቆርጦ ሳይላክ ለ24 ሰዓታት የሚቆይ ከሆነ ኪሳራ ነው፤ በመሆኑም መብራት በየጊዜው ስለሚቆራረጥብን የምናወጣውን ወጭ ሳይሸፍን ለኪሳራ የተጋለጥንበት ጊዜ ብዙ ስለሆነ መንግስት ሊደግፈን ይገባል” ብለዋል፡፡ ከባሕር ዳር እስከ ዘጌ ያለው መንገድ የተበላሸ በመሆኑ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ እየተበላሻ መምጣቱ በሚጓጓበት ጊዜ አበባው ላይ ጉዳት እያደረሰ ስለሆነ ምርቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ጥራቱ እንዲቀንስ ማድረጉም ሌላው እንቅፋት ሆኗል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን የመንገድ ግንባታውን በማስጀመራቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ሊኖረው እንደሚችል በአማራ ክልል የኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የፕሮሞሽን እና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይኼነው ዓለም ተናግረዋል፡፡ ይህም ከአበባ ልማቱ ወደ ከተማ እና ከከተማ ወደ አበባ ልማቱ የሚተላለፍበትን የዘጌ መስመር ብልሽት ሊያስተካክለው ይችላል፡፡
የመብራት ችግሩ ክልላዊ ነው ያሉት አቶ ይኼነው ባሕር ዳርን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የኃይል ማከፋፈያ ማዕከላት እየተገነቡ ስለሆነ የአበባ ምርቶችም ሆነ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል ምንጭ እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡ “በተለይ በአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ለተሰማሩ ኩባንያዎች የተጀመረው የኃይል ማሰራጫ ሲጠናቀቅ ቀጥታ የሆነ የመብራት አገልግሎት የሚያገኙ ይሆናል፤ ሥራውም ጣና ፍሎራን ጨምሮ ባሕር ዳር አካባቢ ለሚገኙ አምስት የአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ አምራቾችን ያገናዘበ በመሆኑ የኃይል መቆራረጥን ሊያስቀር ይችላል” ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

አበባ እና ፍራፍሬ የሚያመርቱ ኩባንያዎችን ለማበረታታት የፌዴራል መንግስት ከክልሉ ጋር በመሆን በ2010 ዓ.ም አምራቾቹ ከባሕ ዳር ወደ አውሮፓ የቀጥታ በረራ እንዲያደርጉ ታስቦ የግዙፍ የጭነት አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያም ተሰርቶ የአበባ ምርቶች ከባሕር ዳር ወደ አውሮፓ በቀጥታ እንዲላኩ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አምስቱ የአበባ አምራች ኩባንያዎች ተቀናጅተው በሳምንት ሁለት ቀናት 30 ቶን አበባ ማቅረብ ባለመቻላቸው የቀጥታ በረራው ቀጣይ መሆን እንዳልቻለ ታውቋል፡፡ 
ክልሉ ችግሩን ለመፍታት አምስት የሆላንድ የአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ አምራች ድርጅቶች በቁንዝላ አካባቢ ሥራ እንዲጀምሩ እየተሰራ ነው፡፡ ኩባንያዎቹ ማምረት ሲጀምሩ በማቀናጀት የቀጥታ በረራው ሊጀምር እንደሚችልም ነው የክልሉ የኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ያስታወቀው፡፡

ኩባንያዎቹ ለሚያስገቡት ግብዓት የአማራ ክልል ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስፈላጊውን ትብብር እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው አቶ ይኼነው የነገሩን፡፡ 
በክልሉ ተገንብተው ሥራ የተጀመረባቸው እና እየተገነቡ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም የሥራ ዕድል መፍጠሪያ፣ የቴክኖሎጂ ማሸጋገሪያ እና የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ እንዲሆኑ ታስቦ እየተሰራ እንደሆነ ቢሮው አስታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

Previous articleበኬንያ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራን እየጎበኙ የነበሩ ሰዎች በጎርፍ መወሰዳቸው ተሰማ፡፡
Next article‹‹አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም!›› ኢትዮጵያዊያን