
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ፣ ስልጣንና ተግባር መወሰኛ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ ሰሚ መድረክ እየተካሄደ ነው።
ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) ለሕብረተሰብ ለውጥ የሚተጋው አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን ለማደግ እየሠራ ነው። በዚህ ወቅትም የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ፣ ስልጣንና ተግባር መወሰኛ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶለት ውይይት እየተደረገ ነው።
በባሕር ዳር እየተካሄደ ያለው የሕዝብ ሰሚ መድረክ የተዘጋጀው በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት ነው።
በውይይቱ ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሉባባ ኢብራሂም የተቋሙን ተደራሽነትና የዘገባ ሽፋን አድማስ ለማሳደግ በረቂቅ አዋጁ ላይ ግብዓት ለማግኘት ጉባኤው አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ከመድረኩ መገናኛ ብዙኃኑ የሕዝብን ፍላጎት እንዲያረካ የሚያደርግ ሀሳብና አስተያየት እንደሚገኝበትም አመላክተዋል።
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የሕግ ባለሙያ በጊዜው ገነት የአሚኮን የማሻሻያ አዋጅ አስፈላጊነት አቅርበዋል። በጉባዔው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የሕግ አማካሪ አቶ መርሐጽድቅ መኮንን፣ የድርጅቱ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።
አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በአምስት ሚዲየሞች እና በአምስት ቋንቋዎች ለሕዝብ ተደራሽ ለመሆን በፈታኝ ወቅት ጭምር ስምሪት ወስዶ የሕዝብ ድምፅ ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ ተቋም ነው።
አብመድ ሙያዊ መርሕን መሰረት ባደረገ መልኩ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፓለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል። የድርጅቱ ዘገባዎችም በፍትሐዊነት፣ በተዓማኒት እና በገለልተኛነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
