
በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ 31 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከየካቲት 19 እስከ 25/2013 ዓ.ም ባሉት አንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ግምታዊ ዋጋቸው 31 ሚሊዮን 82 ሺህ 760 ብር ያወጣሉ የተባሉ ልዩ ልዩ የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያጓጉዙ የነበሩ 16 ተሽከርካሪዎችና 17 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በተመለከተ
• በገቢ ኮንትሮባንድ 27 ሚሊየን 309 ሺህ 350 ብር
• በወጪ ኮንትሮባንድ ደግሞ 3 ሚሊዮን 773 ሺህ 410 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡
የተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች የተለያዩ አልባሳት፣ኤሌክትሮኒክስ፣ የብር ጌጣጌጥ፣ ኮስሞቲክስ፣ መለዋወጫ፣ ምግብ ነክ ሸቀሸቀጥ፣መድኃኒት፣የተለያዩ መሳሪያዎችና ልዩ ልዩ ተተኳሽ ጥይቶች፣የዝሆን ጥርስ፣ የኢትዮጵያን ብር ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ፣ አደንዛዥ እጽ፣ ቡናና ሌሎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በተለያዩ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አማካኝነት እንደተያዙ ተገጿል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የጉምሩክ ሠራተኞች ፣የፌደራልና የክልል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ሕብረተሰቡ በጋራ በመሆን በፍተሻና በጥቆማ የተያዙ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
ሕብረተሰቡና አጋር አካላት የኮንትሮባንድን አስከፊነት ተረድተው ኮንትሮባንድን ለመከላከል እያደረጉ ላለው ጥረትና አስተዋጽኦ የገቢዎች ሚኒስቴር ምስጋናውን አቅርበዋል፡፡ ሕብረተሰቡና አጋር አካላት የኮንትሮባንድን በመከላከል እያደረጉ ያሉትን ጥረታቸውንና አስተዋጾኦቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም የገቢዎች ሚኒስቴር ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
