በኬንያ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራን እየጎበኙ የነበሩ ሰዎች በጎርፍ መወሰዳቸው ተሰማ፡፡

148

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 27/2011 ዓ.ም (አብመድ) በአደጋው የሁለት ሰዎች ህይዎት አልፏል፤ የቀሪዎችም ቢሆን ያሰጋል ብሏል ፖሊስ፡፡

ውብ እና ልዩ መልከዓ ምድራዊ ገጽታን የተላበሰ የጎብኝዎች መዳረሻ ሥፍራ ነው፤ ሄልስ ጌት ተብሎ የሚጠራው የኬንያ ብሔራዊ ፓርክ፡፡ በተለይም ደግሞ በውስጡ ገባር ወንዞች የሚጋልቡበት ሸለቋማው ክፍል በውስጡ ለማለፍ የሚያስፈራ ግን ደግሞ የሚያጓጓ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ እናም በኬንያውያኑም ሆነ በውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ተመራጭ መዳረሻ ሥፍራ ነው፡፡

ኬንያን ለመጎብኘት ሲያስቡ ብዙዎቹ ቀድመው ማየት የሚፈልጉት እና የሚመኙት ቦታ ስለመሆኑም ነው በዘገባው የተመላከተው፡፡ በመሆኑም ሥፍራው ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍም የጀርባ አጥንት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሄሊስ ጌት ብሔራዊ ፓርክ አብዛኞቹ ኬንያውያን እና የውጭ ሀገር ዜጎች ደጋግመው ቢያዩት የሚመርጡት ስፍራ እንደሆነም ነው በዘገባው የተመላከተው፡፡

ከሰሞኑ ታዲያ ኬንያውያን እና የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ሰብሰብ በማለት በዚህ ጥብቅ ስፍራ ለመዝናናት ቢያቀኑም መልካም ነገር ግን አልገጠማቸውም፡፡ የጉብኝት ቡድኑ አባላት በጥብቅ ስፍራው ውስጥ ደስታቸውን አጣጥመው ሳይጨርሱ ድንገተኛ ዝናብ ተከሰተ፡፡ የዝናቡ መጠን ከፍተኛ በመሆኑም ጎብኝዎችን ጠራርጎ ወሰደ፡፡

በድንገተኛ አደጋው ከቡድኑ አባላት ውስጥ ሁለቱ መሞታቸው ሲረጋገጥ አምስቱ ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም የሚል ዜናም ተሰማ፡፡ የአካባቢው ፖሊስ ግን የጠፉትም ቢሆኑ በሕይዎት ስለመኖራቸው ሥጋቱን ለአጃንስ ፍራንስ ፕረስ አስታውቋል፡፡

ከኬንያ የዱር እንስሳት አገልግሎት የተገኘ መረጃ እንዳመላከተው በሄሊስ ጌት ብሔራዊ ፓርክ የተፈጠረው ክስተት ለአደጋ ያጋለጠው አምስት ኬንያውያንን እና የውጭ ሀገር ዜጎችን ነው፡፡ በ1984 (እ.አ.አ) የተቋቋመው ፓርኩ ሦስት የጂኦተርማል ጣቢያዎች በውስጡ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ

በምስጋናው ብርሃኔ

Previous articleእስራኤል በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ እና በጸጥታ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናገሩ፡፡
Next articleአምስት የአበባ አምራች ኩባንያዎች ተቀናጅተው በሳምንት ሁለት ቀናት 30 ቶን አበባ ማቅረብ ባለመቻላቸው የቀጥታ በረራው አልቀጠለም፡፡