የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሀገራዊ ምርጫው ሚናቸውን እንዲወጡ እየተሠራ ነው፡፡

217
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሀገራዊ ምርጫው ሚናቸውን እንዲወጡ እየተሠራ ነው፡፡
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) በፖለቲካው ዘርፍ የሚሠማሩ ድርጅቶች ሚናቸውን በተገቢው መልኩ እንዲወጡ እየተሠራ መሆኑን የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጄንሲ አስታውቋል፡፡
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እና በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የማድረግ ሚና እንደሚኖራቸው ታምኗል፡፡
የቀድሞው የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ድርጅቶቹ በፖለቲካው ዘርፍ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የሚገድብ እንደነበር ኤጄንሲው አስታውቋል፡፡
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 13/2011 ዓ.ም ተሻሽሎ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ ግን በምርጫ ቦርድ በአዋጅ የተቀመጠውን መስፈርት ለሚያሟሉ ሀገር በቀል ድርጅቶች ብቻ የመራጮች ትምሕርት በመስጠት፣ በምርጫ ታዛቢነት እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማወያየት እንዲሳተፉ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ እንዳሉት በፖለቲካ ዘርፉ የሚሳተፉ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውግንና ነጻ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የመራጮች ትምህርት መስጠት እንዲችሉ ሕጋዊ ሰውነት ላላቸው ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የትምህርት ተቋማት የማስተማር ፈቃድ ይሰጣል፤ አሁንም በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
መራጮችን ማስተማር የሚፈልግ ድርጅት ቅድሚያ ከቦርዱ ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅበታል፤ ፈቃድ ለማግኘት ደግሞ በሕግ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ወይም እውቅና ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም፣ ቦርዱ ለመራጮች ትምህርት ያወጣውን መስፈርት የሚያሟላ፣ ተግባሩን ለመወጣት የሚያስችል ብቃት ያለው እንዲሁም ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ገለልተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት የመራጮች ትምህርት ስለሚሰጡ አካላት፣ ትምህርቱ ስለሚሰጥበት አሠራር እና ለነዚህ አካላት የማስተማር ፈቃድ አሰጣጥ እና ሥነምግባርን ለመደንገግ መመሪያ አውጥቷል።
የሲቪክ ድርጅቶች ተግባርም በመመሪያና ደንቡ ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆን እንደሚገባው ነው አቶ ፋሲካው ያስታወቁት፡፡ በቦርዱ ፈቃድ በተሰጣችው ተቋማትና ድርጅቶች የሚሰጥ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት እና ስልጠና ቦርዱ በሚያዘጋጃቸው የማስተማሪያ ሰነዶች ላይ መሠረት ያደረገ ይሆናል፡፡
አብመድ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የአሠራር ሥርዓቱን ተከትለው ሚናቸውን እንዲወጡ ኤጄንሲው እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ጠይቋል፡፡
አቶ ፋሲካው እንዳሉት የድርጅቶች ተሳትፎ ትርጉም ያለው ውጤት እንዲያስገኝ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ኤጄንሲው ዕቅድ አዘጋጅቶ እየሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል፤ በሕግና መመሪያው መሠረት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም በትኩረት ይከታተላል ነው ያሉት፡፡
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሀገራዊ ምርጫው ሚናቸውን እንዲወጡም እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ለሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥሩ አመለካከት እንዳለው የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ድርጅቶችም የተቀመጠውን መስፈርት አክብረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleለትግራይ ክልል ከውጭ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶችና ሀገራት በኩል የሚጠበቀው እርዳታ በጊዜ ባለመድረሱ መንግሥት እስካሁን 40 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
Next articleታክስ ማጭበርበር የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡