በሁሉም ተቋማት ከሥልጠና የተገኘውን ለውጥ ከመመዘን ይልቅ ሥልጠናን እንደግብ መውሰድ ይስተዋላል ተባለ፡፡

125
በሁሉም ተቋማት ከሥልጠና የተገኘውን ለውጥ ከመመዘን ይልቅ ሥልጠናን እንደግብ መውሰድ ይስተዋላል ተባለ፡፡
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2013 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም እየገመገመ ነው፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የሴቶች፣ ወጣቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ፣ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እና የአማራ ብዙኃን መገናኛ ደርጅትን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ገምግሟል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከተቀመጡ ግቦች አንፃር የየተቋማቱን አፈፃፀም በጥንካሬ እና በእጥረት እንዲሁም የቀጣይ ጊዜ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን የተመረጡ ጉዳዮች ለመለየት ግምገማው አስፈላጊ ነበር ብለዋል የሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሉባባ ኢብራሂም፡፡
የተቋማቱ የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በተቋማቱ ሪፖርት ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሉባባ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሦስት ዞኖች፣ በስድስት ወረዳዎች፣ በሦስት ከተማ አስተዳደሮች እና በ13 ቀበሌዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
በመስክ ምልከታው የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉም ተጠቁሟል፡፡ የአብዛኞቹ ተግባራት አፈፃፀም ከተያዘው እቅድ አንፃር የተሻለ ሆኖ መገኘቱ በጥንካሬ የሚገለፅ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
በተለያየ ደረጃ ሊገለፁ የሚችሉ ልዩ ልዩ አጫጭር እና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎችን በመስጠት የፈፃሚዎችን አቅም ለማጎልበት የተደረገው ጥረት አበረታች ነበር ያሉት ወይዘሮ ሉባባ በሁሉም ተቋማት ከሥልጠና የተገኘውን ለውጥ ከመመዘን ይልቅ ስልጠናን እንደመጨረሻ ግብ መውሰድ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአሜሪካ የሚገኘው ወንፈል የተሰኘ ተራድዖ ድርጅት ከ900 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ለህሙማን የኦክስጂን መርጃ አገልግሎት የሚሰጥ መሣሪያ ድጋፍ አደረገ።
Next articleለትግራይ ክልል ከውጭ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶችና ሀገራት በኩል የሚጠበቀው እርዳታ በጊዜ ባለመድረሱ መንግሥት እስካሁን 40 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አስታወቀ፡፡