
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 26/2011 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር) እና የእስራኤሉ አቻቸው ቤንያሚን ኔታንያሁ በእስራኤል ተወያይተዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ያወሱት ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀገራቸው በግብርና፣ በጸጥታ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ እና በሌሎችም ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ ተናግረዋል፡፡ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከልም ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሰራ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያካሄደቻቸው ያሉት ምጣኔ ሀብታዊ ለውጦች ለአፍሪካ ምሳሌ እንደሚሆኑም ነው ቤንያሚን ኔታንያሁ የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶር.) ባነሱት ሀሳብም የኢትዮጵያ እና የእስራኤል ትስስትር ዘመናትን የተሻገረ ስለመሆኑ አውስተዋል፡፡ ኔታንያሁ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ፓርላማ ፊት ቀርበው ያደረጉት የአብሮነት መልዕክትም የማይረሳ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በጤና፣ በቱሪዝም፣ በአይሲቲ እና በግብርና ዘርፎች እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር እንድትሰራ ፍላጎት መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ (ዶር.) ገልጸውላቸዋል፡፡ በዚህ ዓመት በእስራኤል እና በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች ህይዎታቸውን ላጡ ወገኖችም የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን የገለጹት ዶክተር ዐብይ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በእስሳት እየተቃጠለ በነበረበት ወቅት እስራኤን የእሳት አደጋ መከላከል ልዑኳን በመላክ ፓርኩን ለመታደግ ያደረገችውን ድጋፍም ኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ እንደምስሰጠው ዶክተር ዐብይ ለኔታንያሁ ነግረዋቸዋል፡፡
አካባቢያዊ እና የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጎልበት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ሀገራት እንዲሰሩ ፍላጎት መኖሩንም ነግረዋቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ፎቶ፡- በጌትነት ገደፋው