
የኢትዮጵያና አሜሪካ ወዳጅነት እንዲጠናከር ተግተው እንደሚሠሩ አዲሷ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓዝን የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጅ ዛሬ ተቀብለዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን አሜሪካ የኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ ወዳጅ ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡ አዲሷ አምባሳደርም በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙት እንዲጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር የወዳጅ ሀገሮች በተለይም የአሜሪካ ትብብር አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አንስተው ውይይት አድርገዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የትህነግ ቡድን ሲፈጥራቸው የነበሩ ችግሮችና በትግራይ ክልል የሕግ የማስከበር እርምጃ የተወሰደበት ምክንያቶች በዝርዝር ለአምባሳደሯ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት ፣ ለመገናኛ ብዙኃን እንዲዘግቡ ሁኔታ መመቻቸቱን አብራርተዋል፡፡ መንግሥት እያደረገ ካለው የ70 በመቶ ሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ ሌሎች በቂ ድጋፍ ሳያደርጉ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የሚሰጡት መግለጫዎች ተገቢነት እንደሌላቸው አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓዝን በቆይታቸው የሁለቱ ሀገሮች ወዳጅነት እንዲጠናከር ተግተው እንደሚሠሩ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a