
ከተሞችን የእድገት ማዕከል ለማድረግ ለ54 ከተሞች ሽግግር መፈቀዱን የአማራ ክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ።
ባሕር ዳር: የካቲት 22/2013 ዓ.ም (አብመድ)
በአማራ ክልል ከተሞችን የእድገት ማዕከል ለማድረግ ለ54 ከተሞች ሽግግር መፈቀዱን የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታውቋል፡፡
ከነዚህ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው በሰሜን ወሎ ዞን የሐራ ከተማ አስተዳደር እውቅና፣ የምስጋናና ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተካሂዷል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ደረጃ የአማራ ክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ኀላፊ ሰኢድ ኑሩ (ዶክተር) የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ችግሮች ሳይገድቡን፤ ልማቱንም ሳንረሳ ብዙ ፈተናዎችን አልፈናል ብለዋል፡፡
ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል ማድረግ አንደኛው ሥራ መሆኑን ያነሱት ኀላፊው በከተሞች ሀብት መፍጠር፣ ከተሞችን ለነዋሪዎቹ ምቹ እንዲሆኑና የስልጣኔ ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዘንድሮ ብቻ ለ54 ከተሞች ሽግግር መፈቀዱን የጠቀሱት ዶክተር ሰኢድ የክልሉ መንግሥት ቢሮው ያቀረበለትን ጥያቄ መቀበሉን ተናግረዋል፡፡
ሽግግሩ ለታዳጊ ከተማነት ከገጠር ማዕከል አስር፣ ከታዳጊ ከተሞች ወደ ንዑስ ማዘጋጃ ቤት አስር፣ ከንዑስ ማዘጋጃ ቤት ወደ መሪ ማዛጋጃ ቤት አራት እና ከመሪ ማዘጋጃ ወደ ከተማ አስተዳደርነት 30 ከተሞችን አሸጋግረናል ነው ያሉት፡፡
ሐራ ከተማ በገቢና በእስትራቴጅካዊ ጥቅሟ የተሻለች መሆኗንም ገልጸዋል። የባቡር መስመሩን በመጠቀም ሰሜኑን ከደቡቡ ለማገናኘት የምታስችል፣ ለወደብ ቅርብ የሆነችና በርካታ ተስፋዎች ያሉባት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ሐራ የወደፊት ትልቅ ማዕከልም ናት ብለዋል፡፡ ከተሞች ከተማ ሁኑ ስላልናቸው ብቻ ከተማ አይሆኑም ያሉት ኀላፊው ለከተሞች እድገት ሀብት መሰብሰብና ሰፋ አድርጎ ማቀድ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ ለሰው ክብር የሚሰጡ ሥራዎችን እንሠራለንም ብለዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37