
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር 580 በመቶ እድገት ማሳየቱን የኢፌዴሪ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
በአማራ ክልል የተሳተፉ ድርጅቶች ከ49 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያንቀሳቅሱ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ አመላክቷል፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በተሰማሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና በክልሉ የመንግሥት ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሠራር በባሕር ዳር ከተማ ተገምግሟል፡፡ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሥራ እንቅስቃሴ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ድርጅቶቹ የኅብረተሰቡን የአኗኗር ሁኔታ በመቀየር፣ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት፣ በመንግሥት በኩል ተደራሽ ያልሆኑ እና በበጀት ውስንነት ያልተከናወኑ የልማት ሥራዎችን በማገዝ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በአማራ ክልል ከ200 በላይ ድርጅቶች በተለያዩ ዘርፎች እየተሳተፉ መሆናቸውን የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶክተር) ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ከ49 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያንቀሳቅሱም ነው የተናገሩት፡፡ ይሁን እንጂ ከሚያንቀሳቅሱት ሀብት አንፃር የተገኘው ውጤት በቂ እንዳልሆነ አመላክተዋል፡፡ ይህንን ለማስተካከልም ከድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ኀላፊው ፕሮጀክቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ከማኅበረሰቡ ጋር የማስተሳሰር ተግባርም ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል፡፡ ለዚህም በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ በኩል ጥሩ አደረጃጀት መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የሀብት መጠንና የተሠማሩበትን ቦታ የመለየት ሥራም መከናወኑንም አስታውቀዋል፡፡ ይህም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ፍትሐዊ ተደራሽነት እንዲኖርና በአግባቡ እንዲመራ እንደሚያግዝ ነው ኀላፊው የገለጹት፡፡
ዶክተር ጥላሁን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የድርጅቶችን መረጃ የሚሰንድ ሶፍትዌር ማበልጸግ እንደተቻለም አመላክተዋል፡፡
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ተሻሽሎ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ የድርጅቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ መጨመሩን የኢፌዴሪ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ ሀገራዊ ለውጥ ከመምጣቱ ቀድሞ በኢትዮጵያ የነበረው የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የአሠራር ማዕቀፍ አሳሪ እንደነበር የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የድርጅቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በእጅጉ ቀንሶ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ መረጃ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት ማሻሻያ ካደረገባቸው ዘርፎች መካከል የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች ጉዳይ አንዱ ነው፤ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሀገረ መንግሥት ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ በማመን በፖሊሲና በስትራቴጂ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፤ ለዚህም የአዋጅ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ማብራሪያ አዋጅ ቁጥር 13/2011 ቀደም ብሎ የነበረውን አሳሪ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የአሠራር ማዕቀፍ ሽሯል፡፡ አዋጁ ከተሻሻለ ጀምሮ የድርጅቶች ቁጥር ከፍተኛ እድገት ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ 1 ሺህ 300 አዳዲስ ድርጅቶች ተመዝግበዋል፤ 1 ሺህ 800 ነባር ድርጅቶች ደግሞ እንደ አዲስ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአጠቃላይ 3 ሺህ 200 ድርጅቶች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የድርጅቶች እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ካለው የመንግሥት መዋቅር ጋር ግንኙነት እንዲያደርጉ አሠራር መዘርጋቱን ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል፡፡ ቅንጅታዊ አሠራሩ መሻሻል ቢያሳይም ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ከመንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን እርስ በራሳቸው ተቀራርበው መሥራት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ